AMN- መጋቢት 27/2018 ዓ.ም
ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታዩት ታላላቅ የረጅም ርቀት ሯጮች መካከል አንዱ ነው።
ኃይሌ ያደገው በገጠር ሲሆን፣ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድና ለመመለስ በየቀኑ 10 ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ ይሮጥ ነበር።
ይህ የልጅነት ልምዱ ለወደፊት የሩጫ ስኬቱ ትልቅ መሠረት እንደሆነለት ይነገራል።
ኃይሌ በስፖርታዊ ውድድሮች ዘመን በርካታ ድሎችንና ክብረ ወሰኖችን አስመዝግቧል።
10ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድርን ጨምሮ በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል።
በዓለም የቤት ውስጥ እና የሜዳ ላይ ሻምፒዮናዎች በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰብስቧል።
ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ርቀቶች የዓለም ክብረ ወሰኖችን ሰብሯል።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከሩጫው ዓለም በይፋ ከተሰናበተ በኋላ፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በመሠማራት ስኬታማ ነጋዴ ለመሆን ችሏል።
በሆቴል፣ በሪል እስቴት፣ በግብርና (ቡና) እና በመኪና መገጣጠሚያ ዘርፎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በትምህርት ቤቶች ግንባታና በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በንቃት ይሳተፋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግሏል።

ኃይሌ ገብረሥላሴ “የማይቻለውን ማድረግ ይቻላል” በሚለው መሪ ቃሉና ሁሌም በማይጠፋው ፈገግታው ይታወቃል።
ለኢትዮጵያ ስፖርትና ኢኮኖሚ ባበረከተው አስተዋጽኦ የሀገር ባለውለታ ተደርጎም ይቆጠራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን አዲስ ስፓርት ፓርክን የመረቁ ሲሆን፣ በዓለም የስፖርት መድረክ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሚዳልያዎችን ላስገኙ ጀግኖች አትሌቶች የክብር ሀውልት ቆሞላቸዋል።
ከእነዚህ መካከል ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በዘርፉ ላበረከተው አስተዋጽኦ የክብር ሃውልት ቆሞለታል።
በወንድማገኝ አሰፋ