የነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ መናር ተጽእኖን ለመቋቋም ሃገራት ምን አይነት የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይሆን?

You are currently viewing የነዳጅ አቅርቦት እና ዋጋ መናር ተጽእኖን ለመቋቋም ሃገራት ምን አይነት የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይሆን?

AMN መጋቢት 28/2018 ዓ.ም

በመካከለኛዉ ምስራቅ የተከሰተዉ ጦርነት ዘላቂ መፍትሔ ባጣበት በአሁኑ ወቅት በርካታ የአለም ሃገራት በነዳጅ አቅርቦት እጥረትና በነዳጅ ዋጋ መናር እየተፈተኑ ይገኛሉ፡፡

ሃገራቱ የነዳጅ አቅርቦት መቆራረጥ እንዳይከሰት እና የዋጋ ንረት ኢኮኖሚያቸውን እንዳያናጋ የተለያዩ ጥንቃቄዎችን እና እርምጃዎችን እየወሰዱ ነዉ፡፡

በኢኮኖሚ የበለጹ ሃገራት በተለይም የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ አባል ሃገራት የአቅርቦት እጥረት ቢከሰት ለተወሰኑ ወራት ሊያቆያቸው የሚችል የነዳጅ ክምችት ያላቸዉ ሲሆን እንደ አሜሪካ እና አውሮፓ ያሉ ሀገራት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ገበያውን ለማረጋጋት ከመጠባበቂያ ክምችታቸው ነዳጅ ወደ ገበያ የማውጣት ዝግጁነት እያሳዩ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ፊታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ እያዞሩ የሚገኙ ሃገራትም አሉ፡፡ አንዳንድ ሀገራት ደግሞ የራሳቸውን የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ቁፋሮ ስራዎችን በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ታዳጊ ሀገራትም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በዜጎቻቸው ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የነዳጅ ድጎማ እና የታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግስታቱ የነዳጅ ዋጋን በከፊል በመሸፈን የችርቻሮ ዋጋ እንዳይጨምር ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን የትራንስፖርት እና የሸቀጦች ዋጋ እንዳይንር የነዳጅ ታሪፎችንም በየጊዜው በመከለስ ላይ ይገኛሉ፡፡

በመካከለኛዉ ምስራቅ የተከሰተዉ ጦርነት በርካታ ሃገራት ከነዳጅ ጥገኝነት ተላቀዉ ወደ ኤሌክትሪክ እና ታዳሽ ኃይል እንዲሸጋገሩ ግፊት እያደረገ መሆኑንም መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ መናርን ተከትሎ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን አጠቃቀም የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች እና ማበረታቻዎች እየተስፋፉ ሲሆን በፀሐይ እና በንፋስ ኃይል ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች እንዲጨምሩም እየተደረገ ነው።

አንዳንድ ሀገራት ደግሞ የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ የተለያዩ መመሪያዎችን በማዉጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀምን በማበረታታት ፤ አስፈላጊ ለሆኑ ስራዎች ብቻ ነዳጅን የመጠቀም እና ብክነትን የመቀነስ ግንዛቤን በመፍጠር ላይ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን አለም አቀፍ ተግዳሮት ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ የምትገኝ ሲሆን በኤሌክትሪክ እና ታዳሽ ኃይል ዘርፍ ቀደም ብላ የወሰደችዉ እርምጃ ለወቅታዊዉ አለም አቀፍ ችግር ብቸኛ መፍትሄ ሆኗል፡፡

መንግስት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስም ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የነዳጅ ድጎማ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን የሕዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀምን ከማበረታታት ጀምሮ አስፈላጊ ለሆኑ ስራዎች ብቻ ነዳጅን የመጠቀም እና ብክነትን የመቀነስ አቅጣጫዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

በሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የሚወሰደዉ እርምጃም ከወትሮዉ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ማህበረሰቡም ይህንን አለም አቀፍ ችግር ለመቋቋም ከመንግስት ጋር በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በመካከለኛዉ ምስራቅ የተከሰተዉ ጦርነት ሀገራት በኢነርጂ ዘርፍ ያላቸውን ደህንነት እንደገና እንዲፈትሹ እና ራሳቸውን ከድንገተኛ የዋጋ መዋዠቅ የሚከላከሉበትን መንገድ እንዲፈልጉ እያስገደደ መሆኑንም እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review