AMN- መጋቢት 28/2018 ዓ.ም
የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ምንም ዓይነት የምርት እጥረት እንዳይከሰትና ነዋሪው ያለ ስጋት በዓሉን ማክበር እንዲችል ሰፊ የገበያ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ለበዓሉ ፍጆታ የሚውሉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለገበያ ማቅረቡን ገልጿል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ለበዓሉ የሚውሉ መሰረታዊ ፍጆታዎች በበቂ ሁኔታ ወደ ከተማዋ እንዲገቡ መደረጉን አረጋግጠዋል። እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ለበዓሉ ገበያ 123 ሚሊዮን እንቁላል፣ 201 ሺህ ኩንታል ጤፍ እንዲሁም 2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ሽንኩርት ተዘጋጅቷል።
ለስጋ ፍጆታ የሚውሉ 1 ሚሊዮን በግና ፍየሎች ለገበያ ዝግጁ መሆናቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ ሀቢባ፤ በተለይም በሸማቾች ማህበራት በኩል አንድ ኪሎ ስጋ በ650 ብር ለህዝቡ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

እነዚህ ምርቶች በከተማዋ በሚገኙ የገበያ ማዕከላት፣ በ840 የሸማች ሱቆች እንዲሁም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 246 የእሁድ ገበያዎች ላይ በስፋት እንዲቀርቡ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም 11ዱም ክፍለ ከተሞች የተዘጋጁ የትንሳኤ በዓል የገበያ ባዛሮች ከዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆኑ ተመላክቷል።
ቢሮው በበዓል ሰሞን የሚስተዋለውን ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በየደረጃው የቁጥጥር ቡድኖችን ማሰማራቱን የገለጹት ኃላፊዋ፤ ከተለጠፈው ዋጋ በላይ በሚሸጡና ህገ-ወጥ ድርጊት በሚፈጽሙ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ የህግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል።
በቴድሮስ ይሳ