በቀጣይ ወራቶች በመዲናዋ ከዚህ በፊት ያልነበሩና አዳዲስ የልማት ስራዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በቀጣይ ወራቶች በመዲናዋ ከዚህ በፊት ያልነበሩና አዳዲስ የልማት ስራዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- መጋቢት 28/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ስፖርት ፓርክ ግንባታ ሂደት ዉስጥ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እዉቅና ሰጥተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ፓርኩ በአይነቱ ልዩ የሆነ አካታች፣ ማንንም ያልዘነጋ፣ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደረገ ልማት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ ለሀገሪቱ ክብርና ዝናን ያጎናጸፉ ጀግኖች አትሌቶች በሕይወት እያሉ እውቅና እንዲያገኙና ያለፉትም እንዲዘከሩበት ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ መሆኑንም አንስተዋል።

ፓርኩ በውስጡ በርካታ ዘመናዊና ባህላዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን የያዘ መሆኑ የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዋና ገንዳ እና የተለያዩ የቤት ውስጥ እና የውጪ ስፖርት መጫወቻዎች፤ምቹ የሩጫ ትራክ እና እስከ 300 መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችል ሰፊ የመኪና ማቆሚያ እና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶች እንዳለዉ ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ ከግንፍሌ እና ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን፣ በኡራኤል አካባቢ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ የሚያስችል የአውቶብስ ተርሚናልን ማካተቱን ጠቁመዋል፡፡

ተርሚናሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በሌሉበት ወቅት ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚውል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምረዉ ገልፀዋል።

ከካዛንቺስ አካባቢ ከአሁን በፊት ከነበሩ የንግድ ድርጅቶች መካከል የተወሰኑት ወደ ስራ መግባት የቻሉበት እና ሌሎችም የስራ እድል እንዲያገኙ የተደረገበት መሆኑንም ነው ከንቲባዋ የተናገሩት።

በመሃል ካዛንቺስ የተገነባዉ ፓርክ አዲስ ልማት ነዉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይዞታዉም የአብዛኛዉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለሚያስችል ተግባር መዋሉንም ጠቁመዋል፡

በቀጣይ ወራቶችም ከዚህ በፊት ያልነበሩና አዳዲስ የልማት ስራዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review