AMN- መጋቢት 28/2018 ዓ.ም
አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ፤ አዲስ ስፖርት ፓርክ መገንባት በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና ለተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ የሚሆን ትልቅ አቅም መሆኑን ገለፀች።
ትናንት በተመረቀው ዘመናዊው የአዲስ ስፖርት ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኘችው አትሌቷ በሰጠችው አስተያየት፤ ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት ብቻ ሲታዩ የነበሩና በጉጉት ይመኙ የነበሩ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ዛሬ በሀገር ውስጥ፣ በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ በተሻለና በዘመናዊ መልክ ተገንብተው በማየቷ የተሰማትን ጥልቅ ደስታ ገልጻለች።
ከስፖርተኞች ሃውልት በላይ ስራው ለህብረተሰቡና በተለይም ለወጣቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው አጽንኦት የሰጠችው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ መድረኮች ቀደም ሲል በተወሰኑ የስፖርት አይነቶች ብቻ ትታወቅ እንደነበር ያስታወሰችው አትሌት ደራርቱ፣ አሁን ግን እንዲህ ያሉ ዘመናዊ ማዘውተሪያዎች በመስፋፋታቸው በልዩ ልዩ የስፖርት ዘርፎች ሀገርን የሚያስጠሩ ብቁ ስፖርተኞች ይገኙበታል የሚል ትልቅ ተስፋ እንዳላት ተናግራለች።
አዲስ አበባም “እንደ ስሟ አዲስ ሆናለች” ስትል የከተማዋን እድገት አድንቃለች።

ይህ የስፖርት ፓርክ ለነባር ስፖርተኞች አስተዋፅኦ ሃውልት በማቆም እውቅና የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለነገዎቹ ተተኪዎችም ትልቅ ምሳሌ መሆኑን ደራርቱ ገልጻለች።
ፓርኩ ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ብዙ ወጣቶችና እንግዶች እንደሚጎበኙት የጠቀሰችው አትሌቷ ፤ ወጣቶች እርስ በርሳቸው ተሞክሮ በመለዋወጥ የሀገሪቱን ስም ከፍ የሚያደርጉበት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግራለች።
አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ ለፓርኩ ግንባታ መሳካት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለከተማዋ ከንቲባ በስፖርት ቤተሰቡ ስም ምስጋናዋን አቅርባለች።
በታደሠ ሽፈራው