የአሜሪካ ሴናተሮች ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ የሰነዘሩትን ዛቻ የጦር ወንጀል ነው ሲሉ አወገዙ

You are currently viewing የአሜሪካ ሴናተሮች ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ የሰነዘሩትን ዛቻ የጦር ወንጀል ነው ሲሉ አወገዙ

AMN-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን ሰርጥ ካልከፈተች በመሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ በተደጋጋሚ በመዛት ላይ ይገኛሉ።

ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ሰርጥ ውጥረት ምክንያት የዓለም የኃይል ዋጋ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት በኢራን የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ኢላማ እንደሚያደርጉ ዝተዋል።

የአሜሪካው ሴናተር ክሪስ መርፊ፣ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ እያባባሱት የመጡትን ዛቻ አጥብቀው የኮነኑ ሲሆን፥ በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የታቀዱት ጥቃቶች “የጦር ወንጀል” ከመፈጸም ጋር እኩል እንደሆኑ አስጠንቅቀዋል።

ይህ ተቃውሞ የመጣው ቴህራን የሆርሙዝ ሰርጥን ካልከፈተች ትራምፕ የኢራንን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና ድልድዮች ኢላማ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

ሴናተር ክሪስ መርፊ ይህ እርምጃ በሲቪል ማህበረሰቡ ሕይወት ላይ አስከፊ ጉዳት ያደርሳል ብለዋል።

በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎችን ከመጉዳታቸዉ ባሻገር የተቀመጠለትን ግብ ማሳካት እንደማይችሉ አስጠንቅቀዋል።

ድልድዮችን እና የኃይል ማመንጫዎችን ማፈንዳት ግልጽ የሆነ የጦር ወንጀልም ነው ያሉት።

ሌሎች ታዋቂ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም ትችቱን ተቀላቅለዋል።

ሴናተር በርኒ ሳንደርስ እና የሴኔቱ አብላጫ ድምጽ መሪ ቹክ ሹመር የትራምፕን ንግግር የነቀፉ ሲሆን፥ ሴናተር ኤሊሳ ስሎትኪን ደግሞ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች በዘርፉ የወጡ ሕጎችን የሚጥሱ መሆናቸውን አስጠንቅቀዋል።

የኮንግረስ አባል ያሳሚን አንሳሪ የትራምፕን ንግግር የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ስትል የጠራችው ሲሆን፥ የቀድሞዋ የኮንግረስ አባል ማርጆሪ ቴይለር ግሪን ደግሞ ስልቱ ስትራቴጂካዊ ግቦችን ከማሳካት ይልቅ የኢራን ሲቪሎችን ይጎዳል በማለት መከራከራቸዉን ቲአርቲ ዘግቧል።

በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ያለው ውጥረት የዓለም የነዳጅ ዋጋን ማናሩን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ትራምፕ ባለፉት ጥቂት ቀናት ሰፋ ያሉ ጥቃቶችን እንደሚፈጽሙ በመዛት ማስጠንቀቂያቸውን ደጋግመውታል።

ድርጊቱን ያልተቀበሉ አካላት እንደሚሉት ከሆነ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረግ የጅምላ እልቂት ብቻ ሳይሆን ግጭቱን በማስፋት ዓለም አቀፍ አለመረጋጋትን ሊያባብስ የሚችል አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review