AMN – መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚታዩ የጤና እክሎች መካከል አንዱ የሆነው የሳምባ ቲቢ ስርጭት፣ አሁንም ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።
የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሚካኤል ዳዊት፤ በሽታው ከአየር ወለድ ስርጭቱ ባለፈ፣ የመድኃኒት መላመድ ጋር ተያይዞ እየፈጠረ ያለው ስጋት አሳሳቢ መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ዶ/ር ሚካኤል ስለ በሽታው ባህሪ በሰጡት ማብራሪያ፣ ቲቢ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣና ከአንድ ታካሚ ወደ ጤነኛ ሰው በአየር አማካኝነት በቀላሉ የሚተላለፍ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ሕመምተኞች በሚያስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ወቅት ባክቴሪያው ወደ አየር በመበተን ለሌሎች የጤና ስጋት እንደሚሆን ዶ/ር ሚካኤል ጠቁመዋል።
ታካሚዎች ወደ ሕክምና ከመምጣታቸው በፊት ሊያስተውሏቸው የሚገቡ ምልክቶችን ያብራሩት ዶክተሩ፣ ከ90 በመቶ በላይ በሚሆኑ ታካሚዎች ላይ አክታ ያለው ሳል እንደሚታይና በ30 በመቶ ያህሉ ላይ ደግሞ ከአክታው ጋር ደም ሊቀላቀል እንደሚችል ገልጸዋል።
በምሽት የሚከሰት ከፍተኛ ላብ፣ ትኩሳት እና ያለምክንያት የሰውነት ክብደት መቀነስ የበሽታው ዋነኛ መገለጫዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም በተደረገ ጥናት ከፍተኛ የቲቢ ጫና ካለባቸው 22 የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ዶክተር ሚካኤል፣ የኤች አይ ቪ ስርጭት ከቲቢ ጋር የመከሰት ዕድሉን በአሥር በመቶ ያህል እንደሚያሳድገውም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
መደበኛው የሳምባ ቲቢ ሕክምና ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት አራት ዓይነት መድኃኒቶች፣ በቀሪዎቹ አራት ወራት ደግሞ ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች ለታካሚዎች ይሰጣል ብለዋል።

ሆኖም ታካሚዎች መድኃኒታቸውን በአግባቡ ካልወሰዱ ባክቴሪያው ራሱን ወደ መድኃኒት መላመድ ደረጃ እንደሚሸጋገር ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል እስከ 18 ወራት ይወስድ የነበረው የኤምዲአር ሕክምና በአሁኑ ወቅት በአንድ ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ቢቻልም፣ አሁንም ምንም ዓይነት መድኃኒት የማይበግራቸው የቲቢ ዓይነቶች ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ምልክቶቹ ሲታዩ ፈጣን ምርመራ እንዲያደርግና የታዘዘለትን መድኃኒት በአግባቡ እንዲከታተል ዶክተር ሚካኤል አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው