AMN- መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውና በ1954 ዓ.ም የወጣው የቆየው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ከቀናት በፊት በአዲስ መተካቱ ይታወሳል፡፡
ያታዲያ የአዲሱ ሕግ አስፈላጊነትና ይዟቸው ስለመጣው ዓበይት ለውጦች እና ስላካተታቸው ጉዳዮች በፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ስነ-ስርአትና የማስረጃ ህግ ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግሥት ማህቤ ከኤ ኤም ኤን 24/7 ባደረጉት ቆይታ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሕጉን ለምን መለወጥ አስፈለገ?
ከዘመኑ ጋር አለመሄዱ የቆየው ሕግ አሁን ካለው የቴክኖሎጂ እድገት፣ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ጽንሰ-ሀሳብና ማህበራዊ ለውጥ ጋር አብሮ የማይሄዱ በርካታ ክፍተቶች ነበሩት።
ሌላኛው የሕጎች አለመጣጣም ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም የወጣው አዲሱ የወንጀል ሕግ ቢኖርም፣ እሱን የሚያስፈጽመው ሥነ-ሥርዓት ግን ለረጅም ጊዜ ሳይሻሻል ቆይቷል።
ታዲያ እስካሁን ለምን ዘገየ?
ሕጉ እጅግ ሰፊ 9 መጻሕፍትና ከ400 በላይ አንቀጾች ያሉት በመሆኑ ጥልቅ ጥናትና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን መመልከት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡
ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ማለትም ዳኞችን፣ ፖሊሶችንና የፍትሕ አካላትን ያሳተፈና ስምምነት የተደረሰበት እንዲሆን በመደረጉ 15 ዓመታትን ወስዷል።
ዓበይት ለውጦች፡-
እስካሁን ባለው አሠራር፣ አንድ ሰው ባልፈጸመው ወንጀል ለምሳሌ ሰው ገድለሃል ተብሎ የተፈረደበት ሰው በሕይወት ቢገኝ በስህተት ተፈርዶበት ቢታሰር፣ ነጻ የሚወጣው በ”ይቅርታ” እንጂ በፍርድ ቤት አልነበረም። አዲሱ ሕግ ግን ፍርዱ በሕግ ተከልሶ ግለሰቡ በክብር ነጻ የሚሆንበትን ሥርዓት ዘርግቷል።
ከዚህ ቀደም ፖሊስ ለምርመራ የሚጠይቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ገደብ ስላልነበረው ለሰብዓዊ መብት ጥሰትና ለእንግልት ይዳርግ ነበር። አዲሱ ሕግ ግን ተጠርጣሪው ሳይታሰር ምርመራ እንዲከናወን እንደ መርህ ያስቀምጣል።

እንዲሁም ለከባድ ወንጀሎች እንኳን ቢሆን የጊዜ ቀጠሮው ከአራት ወር እንዳይበልጥ ገድቧል። ከዚያ የጊዜ ገደብ በኋላ ግን ተጠርጣሪው በዋስትና የመፈታት መብት እንደሚኖረው ነው ሃላፊዋ ያነሱት፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅና የፍትህ ስርአቱን ለማዘመንና ተጠያቂነትነ ለማስፈን አጋዥ ሆኖ መዘጋጀቱን በፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ስነ-ስርአትና የማስረጃ ህግ ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ትዕግሥት ማህቤ በቆይታቸው አንስተዋል፡፡
በያለው ጌታነህ