AMN መጋቢት 29/2018
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጠንካራ የዕድገት አፈጻጸም እንዲመዘገብ ማስቻሉን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስቴር በ18 ወራት የተከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ውጤታማነት የሚገመግም ዝርዝር ሪፖርት ይፋ አድርጓል። ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያደረገ ይገኛል።
የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ተከታታይነት ያለው ዕድገት እያሳየ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል ብለዋል። የኢንዱስትሪ ዘርፉ የኢኮኖሚው ሞተር ሆኖ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ የግብርና እና የአገልግሎት ዘርፎች የላቀ አፈጻጸም እያሳዩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ እርምጃው ካመጣቸው ትልቅ ድሎች አንዱ ላለፉት ዓመታት ፈታኝ ሆኖ የቆየውን የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቀናጀ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ የኑሮ ውድነቱን ጫና በማቃለል ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገቡን አብራርተዋል። የምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ተከትሎ በሀገሪቱ የወጪ ንግድ ላይ ታሪካዊ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው ተወዳዳሪነት በመጨመሩና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ማደጉን ጠቅሰው፤ከዚህ በተጨማሪ የሐዋላ ገቢ፣የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትና የውጭ ምንዛሬ ክምችት ላይ የታየው መሻሻል ከፍተኛ ነው ብለዋል።

መንግሥት የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማዘመኑ ጠቅላላ ገቢው ከፍ እንዲል ማድረጉን ጠቅሰው፤ ይህም የሀገሪቱን የውጭ ዕዳ ጫና በዘላቂነት ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ ማገዙን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተቀናጀ አመራርና በማስረጃ ላይ በተደገፈ ትንታኔ እየተመራ መሆኑን ጠቁመው፤በቀጣይም መዋቅራዊ ለውጦችን በማጠናከር የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡