AMN መጋቢት 29/2018
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ከሀገራዊ ጥቅም ባለፈ ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ደህንነትን በመጠበቅ ለቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ”የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጣና የባሕር አስተዳደር፤ አካታችነትና ትስስር ለጋራ ጥቅም” በሚል መሪ ሃሳብ አራተኛውን ዓመታዊ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ሉዓላዊ መዳረሻ ጥያቄ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ስትራቴጂክ መሰረትና ቅቡልነት ያለው ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከባሕር በር መዳረሻዎቿ የተገለለችበት ኢ- ፍትሕዊ በደልም በቀጣናዊ ጂኦ – ፖለቲካዊ የኃይል ሚዛንና የባሕር ላይ ደኅንነት ጥበቃ የሚጠበቅባትን ገንቢ ሚና እንደገደበው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የህዝብ ቁጥር የልማት ፍላጎት ለማሳለጥም አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የባሕር ኃይል ግንባታም የባሕር ላይ ውንብድና፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ሽብርተኝነትና መሰል ስጋቶችን ለመዋጋት ከፍተኛ የትብብር አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቀይ ባሕርና ኤደን ባሕረ ሰላጤ ሉዓላዊ መዳረሻ ፍላጎትና ጥያቄም ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ደኅንነትን በማረጋገጥ ለቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ብልፅግና የላቀ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ የቀይ ባሕርና ኤደን ባሕረ ሰላጤን ዘላቂ ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳለጥ ሁሉንም ሀገራት የሚያሳትፍ የባሕር ላይ አስተዳደር መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ቀጣናዊ ትስስርን በማጎልበት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም የንግድ መዳረሻ ወደቦችን ኢኮኖሚያዊ አስተሳሳሪ ሰንሰለትነት የሚያገለግሉበትን ወሳኝ የውሃ ላይ የአስተዳደር ሥርዓት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በውይይቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ተጋባዥ ተሳታፊዎች መገኘታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡