AMN-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከዕዳ ጫና ወደ ሥራ ዕድል ፈጣሪነት ተሸጋግሯል ሲል አደነቀ።
የዓለም ባንክ በገጸ-ድሩ ባሰፈረው ዘለግ ያለ ዘገባ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የህዝብ ፈንድን ከመጠቀም ይልቅ ወደ ገቢ ምንጭነት ተሸጋግረዋል ብላል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በግብር እና በትርፍ ክፍፍል በድምሩ 117 ቢሊዮን ብር ለሀገር ውስጥ በጀት ማብረከታውን ነው ባንኩ የጠቀሰው፡፡ ለዓመታት እነዚህ ድርጅቶች ራሳቸውን ለመቻል የሚያስችል በቂ ገቢ አያመነጩም ነበር፤ ለህዝብ ፋይናንስ አስተዋጽኦ ከማድረግ ይልቅ ጥገኞች ነበሩ።
ባንኩ እ.ኤ.አ. በ2021 ያደረገውን ግምገማ ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት የ41 የፌዴራል ልማት ድርጅቶች ገቢና የሀብት መጠን ቢያድግም፣ ትርፋማነታቸው ግን ቀንሶ ነበር። መንግሥት ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ የመንግስት ሀብት አስተዳደር ላይ መሰረታዊ ማስተካከያ ማድረጉን ነው በዘገባው የተጠቀሰው፡፡
መንግስት የትኞቹን ሀብቶች በባለቤትነት እንደሚይዝ ማወቅ፣ ድርጅቶቹ እንዴት እንደሚመሩ መቆጣጠር፣ የፊስካል ስጋቶችን ማስተዳደር እና ድርጅቶቹን ለውጤት ተጠያቂ የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሷል፡፡ የተከናወኑት ማሻሻያዎች የኢትዮጵያን የስራ ዕድል ተስፋ እየቀረጹ መሆናቸውን ነው የዓለም ባንክ በአድናቆት የጠቀሰው፡፡
በተሻለ ሁኔታ የሚመሩና በፋይናንስ የጠነከሩ ድርጅቶች አሁን አገልግሎቶቻቸውን ለማስፋፋትና በአዳዲስ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ችለዋል፤ ይህም በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የክህሎት ልማትና አዳዲስ የስራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ መንገድ ከፍቷል ብሏል።
የዓለም ባንክ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም፣ የኢትዮጵያ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ዘመናዊ የማድረግ ሂደት ጠንካራ የመንግስት አመራር ከተመረጠ ድጋፍ ጋር ሲጣመር ምን ሊሳካ እንደሚችል ማሳያ ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡
አሰራርን በማጠናከርና የመንግስት ሀብቶችን ከልማት ግቦች ጋር በማጣጣም፣ ሀገሪቱ ለስራ ዕድል ፈጠራና በግል ዘርፍ ለሚመራ ዕድገት አዳዲስ መንገዶችን እየከፈተች መሆኗን ነው ዳይሬክተሯ ማርያም ሳሊም የገለጹት፡፡

እስካሁን የታየው መሻሻል ቀጣይነት ያለውና የታቀደ የሪፎርም ጥረት ውጤት ነው ያለው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመንግስትን የንግድ ሀብቶች እንደ አንድ ፖርትፎሊዮ ለማስተዳደር የሀገሪቱ የመጀመሪያው ሉዓላዊ የሀብት አስተዳደር ድርጅት ሆኖ መመስረት ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይህም መንግስት የህዝብ ሀብትን በስትራቴጂካዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያስተዳድር የሚያስችል ትልቅ ተቋም ፈጥሯል ብሏል፡፡
ባንኩ በኢትዮጵያ ፖስታ እና የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የተገኙትን ለውጦችም በአርአያነት ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ከዓመታት ኪሳራና ከኦዲት እዳ ወጥቶ በዘርፉ ጠንካራ አፈጻጸም ካላቸው ድርጅቶች አንዱ መሆኑን ሲገልጽ ፣ የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ በግብርና ንግድ ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን የሚገድቡ እንቅፋቶችን በማስወገድ ላይ እንዲያተኩር አደረጃጀቱን ቀይሯል ብሏል።
በታደሰ ሽፈራው