AMN መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ “ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው 20ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች መክፈቻ ጉባኤ ላይ ተገኝተናል ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) መሪነት የተጀመረው የፖሊስ ሪፎርም፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኃይልን ዘመኑን የዋጀ፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በዕውቀት የዳበረ እንዲሁም ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ መሆን የቻለ ተቋም እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ፖሊሶቻችን – ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቡ እና ለህሊናቸው ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸዋል። “አደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ” ብለው የሚያምኑ እና ሀገር እና ሕዝብ የሰጧቸውን አደራ መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ የሚጠብቁ መሆንም ይገባቸዋል።
የፖሊስ ሀይላችን የጥፋት ኃይሎች በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት በአንድነት በመቆምና መስዋዕትነት በመክፈል ቀልብሷል፤ ይህም ለሁላችንም ኩራት ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የሀገርን እድገት የማይፈልጉ ኃይሎችን ሴራ በንቃት የማክሸፍና በመጭው ግንቦት የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ኃይላችን የላቀ ኃላፊነት አለበት፡፡ መዲናችን ለምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ስኬትም የተለመደ ታሪካዊ ሚናውን ሊወጣ ይገባል።
የፖሊስ አመራሮችና የሠራዊቱ አባላት በዕውቀት፣ በታማኝነትና በሕዝብ አገልጋይነት ስነ-ልቦና ለላቀ ተልዕኮ እንድታዘጋጁ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡