AMN -ሚያዝያ 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባን የአፍሪካ የሥነ-ፈጠራ ማዕከል ለማድረግ ያለመና በክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ ልዩ የሙዚቃ ድግስ የታጀበው የክራፍት አዲስ የሥነ-ፈጠራ ጥበባት ፌስቲቫል ከሚያዝያ 22 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በአድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የሥነ-ፈጠራ ጥበባት ለለውጥ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል፤ በአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን፣ በዘሌማን ኮሚኒኬሽን እና በፍሎውለስ ኤቨንትስ ትብብር የተዘጋጀ ነው። መድረኩ የአፍሪካን የሥነ-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም መቀየርን ቀዳሚ ዓላማው አድርጓል።
በዝግጅቱ መግለጫ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ እንደገለጹት፤ ፌስቲቫሉ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ የከተማዋን የቱሪዝም ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
አዲስ አበባ ለሥነ-ጥበብ የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ለፌስቲቫሉ የሚመጡ እንግዶች የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጎበኙ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።
የዘሌማን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ወልደማርያም በበኩላቸው፤ የክራፍት አዲስ ዋነኛ ግብ የአፍሪካን የፈጠራ ምናብ ከተሰጥኦ ወደ ተቋም፣ ከሥነ-ፈጠራ ደግሞ ወደ ዘላቂ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ የለውጥ መንገዶችን መገንባት ነው ብለዋል።

በአካል ከ10 ሺህ በላይ፣ በዲጂታል አማራጮች ደግሞ እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው የዘንድሮው ፌስቲቫል ልዩ ትኩረት፤ የኢትዮ-ጃዝ አባት ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ 10 አባላት ያሉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ‘Steps Ahead’ ባንዳቸውን ከለንደን በማምጣት ታሪካዊ የሙዚቃ ድግስ ያቀርባሉ።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በዲጂታል ጥበባት እና በቪዲዮ ጨዋታዎች ላይ ያተኮሩ ማስተር ክላሶች ይቀርባሉ። የፈጠራ ባለሙያዎችን በቀጥታ ከገዢዎች ጋር የሚያገናኝ የክራፍት ገበያ ኤግዚቢሽን ይካሄዳል።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ በኢንቨስትመንትና በሥነ-ፈጠራ ኢኮኖሚ ዙሪያ የተለያዩ የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተመላክቷል።
በመሀመድ ኑርዓሊ