ከኪሳራ ወደ ትርፍ፣  የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዲስ ምዕራፍ

You are currently viewing ከኪሳራ ወደ ትርፍ፣  የኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዲስ ምዕራፍ

AMN-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጉዞ ውስጥ ለዓመታት እንደ ትልቅ ተግዳሮት ይታዩ የነበሩት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ አሁን ላይ የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም የሚያጠናክሩ የገቢ ምንጮች መሆን ጀምረዋል።

በ2017/18 የበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ፣ እነዚህ ድርጅቶች 98 ቢሊዮን ብር ታክስ እና 19 ቢሊዮን ብር የትርፍ ድርሻ ለመንግሥት ገቢ አድርገዋል።

ይህ ስኬት ለደሞዝ፣ ለኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ለሕዝብ አገልግሎቶች የሚውል ተጨማሪ ሀብት ከመፍጠሩ ባለፈ፣ በብሔራዊ በጀቱ ላይ የነበረውን ከፍተኛ ጫና አቅልሏል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁኔታው ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነበር። እ.ኤ.አ. በ2021 የዓለም ባንክ ባደረገው ግምገማ፣ ከ2013 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት የድርጅቶቹ ገቢ ቢያድግም ትርፋማነታቸው ግን እያሽቆለቆለ ነበር።

ብዙዎቹ ድርጅቶች ኦዲት የተደረገ የፋይናንስ መግለጫ አልነበራቸውም፤ አንዳንዶቹ ከአምስት ዓመት በላይ ሪፖርት አላወጡም ነበር፤ መንግሥት ስለ ድርጅቶቹ ትክክለኛ ቁመናና ስጋቶች መረጃው አልነበረውም፤ ኪሳራቸው በጠቅላላው የመንግሥት በጀት ውስጥ እንዲዋጥ ይደረግ ነበር።

ይህን ምስቅልቅል ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት አዳዲስ አሠራሮችን ለመጀመር በመወሰኑ  ከእ.ኤ.አ. 2019 ጀምሮ በዓለም ባንክ ድጋፍ የታገዘ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች ተከናወኑ።

በዚህም የገንዘብ ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ የልማት ድርጅቶችን አጠቃላይ የመረጃ ቋት መገንባት ቻለ። ይህም ፖሊሲ አውጪዎች የእያንዳንዱን ኩባንያ ገቢ፣ ወጪ እና ዕዳ በግልጽ እንዲያዩ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም የአፈጻጸም ክትትል የሚያደርግ ልዩ ዳይሬክቶሬት እንዲቋምም ተደረገ፡፡

ሌላው የሀገሪቱን የንግድ ሀብቶች በስትራቴጂካዊ መንገድ ለመምራት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተመሠረተ። ይህም እንደ ሉዓላዊ ሆልዲንግ ኩባንያ በማገልገል የሀብት አያያዝን ወደ ዘመናዊና ሙያዊ አሠራር አሸጋግሯል።

በተጨማሪም በአዲሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሕግ መሠረት፣ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎችን እንዲከተሉ እና በየዓመቱ ኦዲት የተደረገ መግለጫ እንዲያወጡ ተደርጓል። ይህም ከግል ዘርፉ ጋር በፍትሃዊነት እንዲወዳደሩ መንገድ ከፍቷል።

አሁን ላይ ድርጅቶች ከዓመታት ኪሳራ ወጥተው ትርፋማ፣ ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግል ተሳትፎን የሚያበረታታ አዲስ አወቃቀር የዘረጋ ሲሆን፣ የካፒታል ገበያ ዝግጅት ደግሞ የተመረጡ ድርጅቶች አክሲዮኖቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የንብረት አስተዳደር መመሪያ ወጥቶ መሬትና መሣሪያዎችን ጨምሮ የሕዝብ ሀብቶች በሥርዓት መመዝገብ ጀምረዋል።

የእነዚህ ድርጅቶች መጠናከር ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለኢኮኖሚ ሽግግሩ የጀርባ አጥንት ነው። ጠንካራ የፋይናንስ መረጋጋት ያላቸው ድርጅቶች አገልግሎታቸውን ማስፋፋትና በአዳዲስ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ።

ኢትዮጵያ አሁን ትኩረቷን ስጋቶችን ከመቆጣጠር ወደ ዕድሎችን መጠቀም አዙራለች። ይህም የሕዝብ ሀብት ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እንዲሆን ዋስትና ይሰጣል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review