AMN መጋቢት 29/2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ የሚከታተል ቡድን ሥምሪትና ተግባራትን በተመለከተ ትላንት መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ቦርዱ ቀደም ሲል ከመንግሥት የፀጥታ ተቋማትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰበሰቡ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የተለያዩ የምክክር መድረኮችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የዚህኛው ውይይት ዋና ዓላማም የቀረቡት መረጃዎች በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለመፈተሽና የክትትል ቡድኑን የሥምሪት ዝርዝር ተግባራት ላይ ለመመካከር መሆኑን ገልጸዋል።
የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ የቦርዱ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ቀነኒ እንሰርሙ የክትትል ቡድኑ ስለሚሰማራበት አግባብና ዝርዝር ኃላፊነቶች ገለጻ ሰጥተዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች የተውጣጣው ይኸው የክትትል ቡድን በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይወሰን፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች፣ አጠቃላይ የምርጫውን አፈጻጸም እንዲሁም የምርጫውን ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒነት የመታዘብ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በዕለቱ በተካሄደው ውይይት ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ እና ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የክትትል ቡድኑም በዕለቱ በይፋ ተዋቅሮ ሥራውን እንዲጀምር ተደርጓል።
ቦርዱ ከዚህ ቀደም ከክልልና ከተማ መስተዳድሮች፣ እንዲሁም ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር የምርጫ ክልሎችን ወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ተከታታይ ግምገማዎችን ሲያካሂድ መቆየቱንም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
በሌላ በኩል ቦርዱ የመራጮች ምዝገባን ለማቀላጠፍ “በምርጫዬ” የሞባይል መተግበሪያን ይፋ ማድረጉን አስታውቆ፤ መራጮች መተግበሪያውን ከአፕ-ስቶር (App Store) እና ከፕለይ-ስቶር (Play Store) በማውረድ ወይም በቀጥታ በድረ-ገጽ አማራጭ በመጠቀም መመዝገብ እንደሚችሉ ጥሪ አቅርቧል።
የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ተግባራዊ የሚደረግባቸውን የምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ቦርዱ ባወጣው ማስፈንጠሪያ አማካኝነት ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ በቀሪ የምርጫ ጣቢያዎች ግን ምዝገባው በመደበኛው የማንዋል አሠራር እንደሚከናወን ቦርዱ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል።