የሕማማት ሳምንት – የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የታረቀበት የድኅነት ጉዞ

You are currently viewing የሕማማት ሳምንት – የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የታረቀበት የድኅነት ጉዞ

AMN-መጋቢት 30/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት፣ የሕማማት ሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ድኅነት ሲል የተቀበለው መከራ የሚታሰብበት ቅዱስ ወቅት ነው፡፡

ሳምንቱ የሰው ልጅ ካጣው ክብር የተመለሰበትና ከፈጣሪው ጋር ፍጹም ሰላምን ያገኘበት ልዩ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ አዱኛ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ አስገንዝበዋል።

እንደ መጋቢ ሐዲስ ገለጻ፣ ይህ የተቀደሰ ሳምንት ምዕመናን ስለ በደላቸው የሚጸጸቱበትና በንስሐ ወደ ፈጣሪ የሚቀርቡበት ወቅት በመሆኑ ቤተክርስቲያን በንስሐ ጸሎትና በልዩ ልዩ የሕማም ዜማዎች ጌታ ለሰው ልጅ ፍቅር ሲል የከፈለውን ዋጋ ትዘክራለች።

ምእመናንም በየዕለቱ በቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ በመገኘት አምላካዊ መከራውን እያሰቡ በስግደትና በምሕላ የሚያሳልፉ ሲሆን፣ ይህም ከመንፈሳዊ በረከት በተጨማሪ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቁበት የንስሐ መንገድ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያሉት ቀናት እያንዳንዳቸው የራሳቸው የታሪክ መታሰቢያ እንዳላቸው ያስረዱት መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ፤ በተለይም ጸሎተ ሐሙስ የምስጢረ ቁርባን መመሥረቻና እየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ፍጹም ትሕትናን ያስተማረበት ዕለት መሆኑን፣ እንዲሁም ስቅለት ዕለተ ዓርብ የሰው ልጅ የድኅነት ዋጋ በመስቀል ላይ የተከፈለበትና የሰው ልጅ ነጻነት የታወጀበት ታላቅ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሳምንት ምእመናን ከማንኛውም ሥጋዊ ደስታ በመታቀብ፣ ሰላምታ ሳይለዋወጡና በትሕትና በመመላለስ ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ሕይወት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንደሚያዝ አብራርተዋል።

መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ አዱኛ በመጨረሻም ባስተላለፉት መልእክት፣ ምእመናን ይህንን ሳምንት በጾም፣ በጸሎትና በትሕትና በማሳለፍ፣ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ከክፉ ተግባራት በመራቅ ለትንሣኤው ብርሃን ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review