AMN መጋቢት 30/2018
ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረገዉ የመርከቦች እንቅስቃሴ እስካልተገደበ ድረስ፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን መካከል ለሁለት ሳምንታት እንዲቆይ በቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መግባባታቸዉን ገልጸዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በበኩላቸው፣ “በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የሚቆሙ ከሆነ” ቴህራን ውጊያውን ለማቆም እንደምትስማማ አስታውቀዋል።
እስራኤል ትራምፕ በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማቆም ያስተላለፉትን ውሳኔ እንደምትደግፍ የገለጸች ቢሆንም፣ የሁለት ሳምንቱ የተኩስ አቁሙ ሊባኖስን እንደማያካትት አረጋግጣለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነት ላይ ለመድረስ እስከ ምሽቱ 2:00 ድረስ የጊዜ ገደብ አስቀምጠው እንደነበረ ይታወቃል።
ሁለቱን ሃገራት አሁን ወደተደረሰበት ስምምነት እንዲመጡ ፓኪስታን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ትገኛለች።
ፖኪስታን ዶናልድ ትራምፕ የሰጡትን የጊዜ ገደብ ለሁለት ሳምንታት እንዲያራዝሙ ጠይቃለች።
ሁለቱም ወገኖችም በመጪው አርብ በኢስላማባድ በሚካሄደው ውይይት ላይ እንዲሳተፉ መጋበዟን ቢቢሲ ዘግቧል።
በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን መካከል ያለው አለመተማመን ድርድሩን እጅግ አስቸጋሪ እንድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከታወጀ በኋላ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አንድ በርሜል ነዳጅ ከ100 ዶላር በታች እየተሸጠ ይገኛል።
በወንድማገኝ አሰፋ