በማቆያ ማዕከላት የታገዘ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ

You are currently viewing በማቆያ ማዕከላት የታገዘ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ

AMN- መጋቢት 30/2018 ዓ.ም

ልጄን ካርቶን ላይ አንጥፌ እያሳደርኩ ቡና አዞር ነበር፤ ዛሬ ግን እሷ በማዕከል እኔ በስራዬ ነፃ ወጥተናል ፤ የምትለው ባለታሪኳ መቅደስ መንበረ ናት ፡፡

ከስደት መልስ፣ ተስፋ በቆረጠችበትና በሰው ቤት ስራ ያሳለፈችውን አስቸጋሪ ወቅት ነበር ሕይወቷን ለመምራት ቡና ማዞር የጀመረችው።

በዛ አስቸጋሪ የጎዳና ላይ ሕይወት ግን ልጇን ካርቶን ላይ አስተኝታ እያጫወተች ቡና መሸጥ ለአንዲት እናት ልቧን የሚሰብር ነበር፡፡

ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አማካኝነት መቅደስና ልጇ አዲስ ምዕራፍ ጀምረዋል።

ልጄ ዘጠኝ ወር እስኪሞላት ድረስ ዳዴ ማለትም ሆነ መቆም አትችልም ነበር የምትለው መቅደስ ከልጇ ባለፈ እሷም ለከፍተኛ የወገብ ህመም ተዳረጋ ብዙ ሰቃይ አሳልፋለች ።

ከዕለታት ባንዱ ቀን የእሷና የልጇን ታሪክ የቀየረ ክስተት ተፈጠረ፡፡ በጎዳና ሲያልፉ ያዩዋት ግለሰቦች ስለ ሕጻናት ማቆያ ማዕከላት መረጃ ከሰጧት በኋላ ነው።

መረጃውን ተከትላ ልጇን በወረዳዋ ስር በሚገኝ የሕጻናት ማቆያ ማዕከል ካስመዘገበች በኋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት፣ ህጻኗ ዳዴ ማለት ጀመረች፣ መቆምና ወንበር ይዞ መራመድ ጀመረች፣ ዛሬ ደግሞ እንደማንኛውም ህጻን የምትሮጥ፣ የምትዘምርና የዋለችበትን ውሎ ለእናቷ የምታወራ ንቁ ህጻን ሆናለች።

የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ለህጻኗ እድገት ብቻ ሳይሆን ለእናቷም የጤናና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዳገኘች ገልፃለች።

ትልቅ እርካታ ነው ያገኘሁት። አሁን ያለ ምንም ድካም ተሯሩጬ እሰራለሁ። ልጆቻችን እዚህ ሲውሉልን እኛ ደግሞ ሰርተን ራሳችንን መለወጥ አለብን ሰትልም አሁን ላይ የፈጠረባትን የራስ መተማመን ትናገራለች ።

መቅደስ ይህንን ትልቅ ዕድል ላመቻቹት ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባና ለአስተዳደሩ አመራር ምስጋና አቅርባለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ሕጻናትን በአካል፣ በአእምሮና በስነ-ልቦና ለማነፅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ 1ሺህ 068 የሕጻናት ክብከቤ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ይህም እንደ መቅደስ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች ወደ ስራ እንዲሰማሩና ልጆቻቸውም ምቹ የዕድገት አካባቢ እንዲያገኙ እያደረገ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review