በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ምጽዋት የሰጡ፤ ግብይት የፈጸሙ እና ሌሎች የትራፊክ ደንብ የተላለፉ አካላት ተቀጡ

You are currently viewing በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ምጽዋት የሰጡ፤ ግብይት የፈጸሙ እና ሌሎች የትራፊክ ደንብ የተላለፉ አካላት ተቀጡ

AMN- መጋቢት 30 /2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ደህንነቱም የተጠበቀ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ለአደጋ ተጋላጭነት አላቸው ተብለው በተለያዩ 40 የከተማዋ መንገዶች ላይ በተደረገ ቁጥጥር ከ100 ሽህ በላይ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በተለይም ለአደጋ መንሰኤ በሆኑት ከፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከርከሩ የተገኙ 80ሺህ892 አሽከርካሪዎች፣ ከተፈቀደው የአልኮል መጠን በላይ ጠጥተው የተገኙ 1ሺህ 653 አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

የደህንነት ቀበቶ ያላደረጉ 3ሺህ 066 ደንብ ተላላፊዎች እና የጭንቅላት መከላከያ ቆብ ያላስሩ 587 የሞተር ብስክሌተኞችም በደንብ 557/2016 መሰረት እንደጥፋታቸው ደረጃ እንዲታረሙ መደረጉን ወይዘሮ ገነት ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ 7ሺህ 026 አሽከርካሪዎች ስልክ በማነጋገር፤ 36 በተመረጡ የትራፊክ መብራቶች ፣ አደባባዮች ላይ እና በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ምጽዋት የሰጡ እና ግብይት የፈጸሙ 4ሺህ 500 ግለሰቦች: በ110 ለህዝብ ትራንስፖርት ብቻ መቆሚያ ስፍራ (Bus stop) ላይ እንዳይቆሙ በተደረገ ቁጥጥር 25,238 ደንብ ተላላፊዎች በመገኘታቸው መቀጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተያያዘም በ9 ወራት በእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ዙሪያ በተደረገ ቁጥጥር 21 ሺህ 202 እግረኞች በገንዘብ ሲቀጡ: 16 ሺህ 651 እግረኞች ደግሞ ማህበራዊ አገልግሎት እንዲሰጡና በድምሩ በ37 ሺህ 850 እግረኞች ተጠያቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በመንቀሳቀሻ መንገድ ላይ ለረዥም ጊዜ ተበላሽተው የቆሙ 743 መኪኖች በክሬን ተነስተው መንገዱ ለትራፊክ ፍሰቱ ምቹ አንዲሆን የማድረግ ስራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ገልፀዋል ፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review