የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች

You are currently viewing የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታዎች

AMN-መጋቢት 30/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይከናወናሉ። የስፔን ሃያላኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ከ ባርሰሎና እንዲሁም ፓሪሰን ዠርማ ከ ሊቨርፑል የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው።

በውድድር ዓመቱ 15 ሽንፈት የገጠመው ሊቨርፑል ወደ ፓርክ ደ ፕሪንስ ተጉዞ ፓሪሰን ዠርመ የሚገጥምበት ጨዋታ በተለይ ለአሰልጣኙ አርነ ስሎት እጅግ ወሳኝ ነው። ኔዘርላንድሳዊው አሰልጣኝ በመጀመሪያ የውድድር ዓመታቸው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አንስተው በሊቨርፑል ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ቢገቡም ፣ ዘንድሮ ግን የሚያሞግሳቸው የለም።

በፕሪሚየር ሊጉ እያስመዘገቡት ያለው ደካማ ውጤት ፣ በሳምንቱ መጨረሻ በማንችስተር ሲቲ 4ለ0 ተሸንፈው ከኤፍ ኤ ካፕ ውጪ መሆናቸው መንበራቸው እንዲነቃነቅ አድርጎታል። ስሎት በቻምፒየንስ ሊጉ የተሻለ ውጤት ካላስመዘገቡ የመሰናበት እጣ ሊደርሳቸው እንደሚችል ይገመታል።

በጥሎ ማለፍ ጋላታሳራይን በድምር ውጤት 4ለ1 ማሸነፍ የቻለው ሊቨርፑል በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ሲያከናውን የዛሬው 18ኛው ይሆናል።

የሊውስ ኤነሪኬው ፓሪሰን ዠርማ ባለፈው ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ ባለ ድል የሆነበትን ድንቅ ብቃት ለማሳየት ቢቸገርም አሁንም ጠንካራ ቡድን ነው። በተለይ በጥሎ ማለፍ ቼልሲን በድምር ውጤት 8ለ2 ያሸነፈበት መንገድ አስወድሶታል።

10ኛ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታውን የሚያደርገው ፓሪሰን ዠርማ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ሊቨርፑልን መግጠሙ ይታወሳል። የፈረንሳዩ ክለብ በሜዳው 1ለ0 ተሸንፎ ፣ በአንፊልድ ግን በተመሳሳይ ውጤት ረቶ በመለያ ምት 4ለ1 በማሸነፍ ነበር ሊቨርፑልን ጥሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው።

ሁለቱ ክለቦች በቻምፒየንስ ሊጉ ሲገናኙ የዛሬ ምሽቱ ለአምስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበራቸው አራት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ድል አስመዝግበዋል።

በዛሬው ጨዋታ በሊቨርፑል በኩል ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ ያገገመው አሌክሳንደር ኢዛክ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል። ፓሪሰን ዠርመ መጠነኛ ጉዳት የነበረበት ብራድሊ ባርኮላን መልሶ ያገኛል። ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ስፔናዊው ዋና ዳኛ ሆሴ ሳንቼዝ ይመሩታል።

ሌላው የምሽቱ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድን ከ ባርሰሎና በካምፕ ኑ ያገናኛል። የስፔን ሃያላን ክለቦች በውድድር ዓመቱ ለአምስተኛ ጊዜ ይገናኛሉ። ባርሳ ባለፈው ቅዳሜ 2ለ1 የረታበትን ጨምሮ በላሊጋው ሁለት ጊዜ አሸንፏል። በኮፓ ዴልሬይ የግማሽ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አትሌቲ በሜዳው 4ለ0 ሲረታ ፣ ባርሳ በካምፕ ኑ የ3ለ0 ድል አስመዝግቦ በድምር ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ይታወሳል።

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ደግሞ ሌላ ቀልብ የሚስብ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ትልቁ መድረክ ላይ አራት ጊዜ ተገናኝተው አትሌቲኮ ሁለቱን ሲያሸንፍ ባርሳ አንድ ድል አስመዝግቧል።

አስገራሚው ከዚህ ቀደም ያደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁሉም የሩብ ፍፃሜ መሆናቸው ነው። በ2013/14 እንዲሁም በ2015/16 በተደረጉ የሩብ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች አትሌቲኮ ማድሪድ በሁለቱም አጋጣሚ በድምር ውጤት አሸንፎ ማለፍ ችሏል።

በታሪካቸው ለሦስተኛ ጊዜ በሩብ ፍፃሜ የሚገናኙበት የዛሬ ምሽት የመጀመሪያ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ይጀምራል።

በጨዋታው በባርሰሎና በኩል ራፊንሃ እና ማርክ በርናል በጉዳት አይሳተፉም። ከጉዳቱ ያገገመው አማካዩ ፍራንኪ ዲዮግ መግባቱ አልተረጋገጠም።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review