የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 አመታት የሀገርን በጎ ገጽታ መገንባት የቻሉ ስኬታማ ስራዎችን ሰርቷል- አቶ መስፍን ጣሰው

You are currently viewing የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 አመታት የሀገርን በጎ ገጽታ መገንባት የቻሉ ስኬታማ ስራዎችን ሰርቷል- አቶ መስፍን ጣሰው

AMN-መጋቢት 30/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 አመታት የገጠሙትን ፈተናዎች ወደ ድል እየቀየረ የሀገርን በጎ ገጽታ መገንባት የቻሉ ስኬታማ ስራዎችን መስራት መቻሉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው የአየር መንገዱን 80ኛ አመት የምስረታ በአልን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በሰጡት መግለጫ በ1938 ዓ.ም በአንድ አሮጌ አውሮፕላን በረራ የጀመረው አየር መንገዱ በተለያዩ ጊዚያት የገጠሙትን ፈተናዎች ወደ ድል በመቀየር አሁን ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ 150 አውሮፕላኖችን በመያዝ በ145 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ ሲመሰረት በአሜሪካዊያን የሰው ኃይል ይተዳደር የነበረውን ስርአት በመቀየር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሀገር ልጆች መተካት መቻሉ የአየር መንገዱን ስኬት ማሳያ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ከዘመናዊ አውሮፕላኖች ባሻገር የሰው ኃይል አቅምን ለማሳደግ የተቋማት ግንባታ መከናወኑን የገለጹት አቶ መስፍን፣ በዚህም የአውሮፕላን አካላትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠግኑ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል፡፡

አየር መንገዱ በ1950 ዓ.ም አቬሽን አካዳሚ ገንብቶ በቂ የሰው ኃይል መፍጠር ተችሏል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ይህም አሁን ላይ በአፍሪካ ስመ ጥር የአቬሽን ማሰልጠኛ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።

ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ለመንገደኞችም አርኪ አገልግሎቶችን ማድረድረስ ተችሏል ብለዋል።

በ2040 በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር መንገዱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ራእይን ይዟል ያሉት አቶ መስፍን፣ አሁን ያለውን ዓለም አቀፍ መዳረሻንና የአውሮፕላኖቹን ቁጥርም ከጥፍ በላይ ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

በአየር መንገዱ የ80 አመት ስኬቶች ውስጥ የአመራሮች እና የሰራተኞች ሚና ከፍተኛ እንደነበርም አቶ መስፍን በመግለጫቸው አንስተዋል።

በሄኖክ ዘነበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review