የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ፋይናንስ ቢሮ በኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ዙሪያ አብሮ ለመስራት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ፋይናንስ ቢሮ በኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ዙሪያ አብሮ ለመስራት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

AMN-መጋቢቴ 30/2018 ዓ.ም

ስምምነቱ የቢሮውን የፋይናንስ ቁጥጥርና አሰራርን ዘመናዊ ለማድረግ ይረዳል ተብሏል፡፡

በስምምነቱ ወቅት ምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ የፋይናነስ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን እንደተናገሩት በከተማዋ በርካታ የልማት ስራዎችን የፋይናንስ እንቅስቃሴን 24 ሰዓት ለመቆጣጥርና ለማስተዳዳር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ትልቅ ሚና እንዳለው አለው ብለዋል፡፡ ስምምነቱ ግልጸኝነትን፤ ተጠያቂነትንና ቀልጣፋ አሰራርን ስለሚያሰፍን የአስተዳድሩን የፋይናንስ ግቦችን ለማሳካት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተመራጭ ማድረጋችን ትክክለኛ አካሄድ ነውም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሆል ሴሊንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር እስክንድር አስፋው በበኩላቸው ባንኩ የሃገሪቱን የዲጅታል ኢትዮጵያ ግብን እውን ለማድረግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝና ይህ ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

99 ከመቶ የሚሆኑት የፌደራል ተቋማት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የፋይናንስ ቢሮም የዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ ኢንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ በ119 ወረዳዎች፤ 600 ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች ስም ያለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ በተማከለ መልኩ በኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ለመስጠትም ስምምነቱ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ባንኩ የውሃና የኤሌክትሪክ ፍጆታ፤ የትራፊክ ቅጣት ክፍያዎች፤ በቤት ልማት እና በሌሎች ዘርፎችም ከአስተዳድሩ ጋር በዲጅታል ባንኪንግ በኩል አብሮ እየሰራ ነውም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በዲጅታል ባንኪንግ አማራጮቹ ከ15.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዳዘዋወረ ተመላክቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review