AMN መጋቢት 30/2018
ኢትዮጵያ በወራት ልዩነት ውስጥ የቀረቡባትን ሁለት ግዙፍ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ክሶች በድል ማጠናቀቋን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት መድረክ ያገኘቻቸውን ሁለት ድሎችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ሀገሪቱ በተከታታይ ያገኘቻቸው እነዚህ ድሎች በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የካሳ ክፍያ ከማዳን ባለፈ የሀገሪቱን ሉዓላዊ ጥቅም ያስጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በተሰጠው ስልጣን መሠረት፣ የሕዝብና የመንግስትን የፍትሐብሔር ጥቅም የማስጠበቅ፣ የፌደራል መንግስት ዋና አማካሪ የመሆን እና በዓለም አቀፍ መድረክ ሀገሪቱ ስትከሰስ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ ዓለም አቀፍ የግልግል ማዕከላት ቢሯቸውን በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ከማድረግ ጀምሮ በውስጥና በውጭ ባለሙያዎች የታገዘ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በድል ከተጠናቀቁት ዋና ዋና ክሶች የመጀመሪያው የቱርኩ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የሆነው Akgun Insaat Makina Sanayii ve Dis Ticaret Ltd. Sti. የተባለው አቅርቦት ከነበረው በድምሩ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክስ መሆኑን ተናግረዋል።
ኩባንያው በለገዳዲና ድሬ ግድቦች አቅራቢያ የኢንዱስትሪ ዞን ለማልማት ፈቃድ ተሰጥቶት እንደነበር ማስታወሳቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡