AMN- መጋቢት 30/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባከናወነው ሰፊ የቁጥጥር ሥራ፣ የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምርቶች እንዲወገዱ ማድረጉን አስታውቋል።
ይህንኑ አስመልክቶም የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ እንጋ እርቀታ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ በመግለጫቸውም፤ 78.3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ምግቦችና መጠጦች፣ 39.6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች እንዲሁም 5.9 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የትንባሆ ውጤቶች መወገዳቸውን ተናግረዋል።

ጥፋት በተገኘባቸው 1 ሺህ 230 የምግብ፣ 187 የጤና እና 68 የመድኃኒት ተቋማት ላይም እንደ ጥፋታቸው መጠን የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የማሸግ፣ የገንዘብ ቅጣትና የብቃት ማረጋገጫ ስረዛ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ሪጀንቶች፣ ያለ ህክምና ማዘዣ መድኃኒት መሸጥ፣ ምንጫቸው ያልታወቁ ምርቶች እና ህገ-ወጥ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች በቁጥጥሩ ወቅት የተለዩ ዋና ዋና ክፍተቶች መሆናቸውን አቶ እንጋ እርቀታ አመላክተዋል።
በታምራት ቢሻው