ኢትዮጵያ እና ጃፓን በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ምክክር አደረጉ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ጃፓን በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ምክክር አደረጉ

AMN መጋቢት 30/2018 ዓ.ም

በጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ልዩ አማካሪ ኦው ሳዳማና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ የተመራ የልዑካን ቡድን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አሰፋ አብዩ (ዶ/ር) እና ከሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች የሚደረጉ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

በውይይቱም ኢትዮጵያና ጃፓን ከዚህ ቀደም በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚሠሯቸውን ተግባራት በማጠናከር በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኛ ቡድኖችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ውይይት አድርገዋል፡፡

እንዲሁም በሳይበርና በአቪዬሽን ደኅንነት ዙሪያ የሚደረጉትን ትብብሮችና የመረጃ ልውውጦች ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮችም መክረዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አሰፋ አቢዩ (ዶ/ር) ፤ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ሪፎርሞችን በተመለከተ ለጃፓን ልዑክ አባላት ገለጻ አድርገዋል። የሪፎርም ሥራዎቹን ፋይዳም አብራርተዋል፡፡

ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አሰፋ ፤ ኢትዮጵያ በሰላማዊ አማራጭ መንገዶች የባሕር በር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ አብራረተዋል።

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦው ሳዳማና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንፃር የሁለቱን ሀገራት ትብብርና አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመረጃና በልምድ ልውውጥ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መስኮች የተጀመሩ የአጋርነት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸውን ጥረቶች ጃፓን እንድምትደግፍ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ያደነቁት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ፤ በአጭር ዓመታት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ሪፎርምና በዓይን የሚታዩ ትላልቅ የከተማ ልማት ሥራዎችን መሥራቷ ለሌሎችም በአብነት የሚወሰድ መሆኑን መግለጻቸዉን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review