የኩላሊት መዘጋት እንዴት ይከሰታል?

You are currently viewing የኩላሊት መዘጋት እንዴት ይከሰታል?
  • Post category:ጤና

AMN- ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም

የኩላሊት መዘጋት የተለያዩ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን በሽንት መስመር የሚከሰት ማንኛውም መዘጋት ኩላሊትን አደጋ ላይ ይጥላል።

በጴጥሮስስ ፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጠቅላላ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪምና የዩሮሎጂ ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር አህመድ አበበ መሀመድ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የኩላሊት ጠጠር በየትኛውም የሽንት መስመር ቦታ ላይ መንቀሳቀስ ካልቻለና ቱቦ ላይ ከተቀመጠ የኩላሊት መዘጋትን እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡

በኢንፌክሽን ምክንያት ወይም በአደጋ ምክንያት የሚመጣ የሽንት ቱቦ መጥበብ፤ ከኩላሊት እስከ ሽንት ፊኛ ያለ ቀጭን የሽንት መስመር ላይ፣ ሽንት ፊኛ ጫፍ ፕሮስቴት ምክንያት መዘጋት ወይም ደግሞ ከሽንት ፊኛ እስከ ሽንት መውጫ ጫፍ ያለው መስመር መዘጋት ነው።

እንዲሁም የሽንት መስመር የትኛውም ቦታ ላይ የሽንት ፊኛ ካንሰር፣ የፕሮስቴት ካንሰር፣ የሽንት ቱቦ ካንሰር ሊሆን ይችላል። እነዚህ እብጠት ስለሆኑ የሽንት መስመርን የመዝጋት እድላቸው ከፍተኛ እንደሆን ገለጸዋል።

ዶክተር አህመድ አበበ መሀመድ፤ ሽንት ከኩላሊት ተመርቶ ወደ ታች በሚወርድበት አካባቢ የኩላሊት እጢ ወይም ካንሰር ካለ የኩላሊት መዘጋትን ይፈጥራል ብለዋል።

የኩላሊት መዘጋት ምልክቶች አንዱ እና ዋነኛው በቀኝ ወይም በግራ ጎን በኩል በጣም ቀስፎ የሚይዝ ለሁለት ለሶስት ቀን በጣም የማያስተኛ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ህመም መሆኑን ገልጻዋል።

ህመሙ በቀኝ ወይም በግራ ጎን ሆኖ አንዳንዴ ወደ ኋላ የሚሄድ ሲሆን የኩላሊት ጠጠር ወደ ሽንት መስመር የገባ ጠጠር ከሆነ ደግሞ አንዳንዴ ወደ ታች ወደ ሽንት ፊኛ የሚሄድ ከባድ የሆነ ህመም ይኖራል ብለዋል።

እንደ ዶክተር አህመድ አበበ መሀመድ ማብራሪያ በጠጠር ምክንያት ኢንፌክሽን ካለ የሽንት መደፍረስ ሊከሰት ይችላል፡፡ እንዲሁም የፕሮስቴት እጢ ወይም የሽንት ፊኛ እጢ የኩላሊት የራሱ እጢ ወይም ካንሰር ካለ ደግሞ ደም ሽንት ላይ ሊኖር ይችላል።

የፕሮስቴት እጢ የሽንት ፊኛ እጢ ከሆነ የሽንት ማስማጥ፣ ማቃጠል፣ ቶሎ ቶሎ መሽናት፣ ሌሊት ለሽንት መነሳት ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።

ምልክቶቹ ሲታዩ መዘናጋት የለብንም ያሉት ዶክተር አህመድ አበበ በተለይ የኩላሊት መዘጋት ህመም ለ 24 ሰዓት ወይንም ለ 48 ሰዓት በጣም ከፍተኛ ሆኖ ከዛ በኋላ በተወሰነ መልኩ የመቀነስና የማዘናጋት ባህሪ እንዳለው አስረድተዋል።

ህመሙ እየቀነሰ ቢመጣም ኩላሊት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀጣይ ሆኖ መጨረሻ ላይ ኩላሊትን እስከ ማጣት ሊያደርስ ስለሚችል ህመሙ እንደተከሰተ ወደ ጤና ተቋም ሄዶ ህክምና ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኩላሊት ጠጠር እንዳይከሰት የሚያደርጉ እንደ ሎሚ፣ ብርቱካን፣ ኪያር የመሳሰሉ ሲትሪክ አሲድ (Citric acid) ንጥረ ነገር ያላቸውን ፍራፍሬዎች መጠቀም እና ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጫት መቃም ማቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review