AMN- ሚያዝያ 1 /2018 ዓ.ም
በበዓላት ወቅት የሚደረግ የይቅርታ ልውውጥ ከሃይማኖታዊ ሥርዓት ይልቅ በማኅበራዊ ልማድ ላይ የተመሠረተ መሆኑን በቀበና መድሃኒዓለም ቤተክርሰቲያን መጋቤ ሰላም ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ከአዲስ ሚዲያ አዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ገልጸዋል።
ቀሲሰ ፋሲል ታደሰ ይቅርታ ለማድረግና ይቅርታ ለመቀበል በዓል ወይም ሰንበት አይጠበቅም፤ ይቅርታ የመዳን፣ የንስሐና የፍቅር መንገድ ነው።
በተለይ ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ ሲነሳ፣ ይቅርታ “ከሞት ወደ ህይወት የመሸጋገር” ያህል ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
ቀሲሰ ፋሲል እንደገለጹት ፈጣሪ ለይቅርታ ቀጠሮ እንደማይሰጥና የሰው ልጅም በማንኛውም ጊዜ ከቂም ነጻ ሆኖ የይቅርታ ሕይወትን ሊለማመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የስነ-ልቦና አማካሪና ስልጠና ባለሙያ ሽመልሰ ገበየው በበዓላት ወቅት የሚደረጉ ይቅርታዎች ለጊዜያዊ ማለፊያ ብቻ ሳይሆኑ፣ ዘላቂ ሰላምን የሚፈጥሩ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የስነ-ልቦና አማካሪዉ ፤ ይቅርታ ማድረግ ከሁሉ በላይ ለራስ የሚሰጥ እረፍት መሆኑን ጠቁመዋል። ቂምና በቀልን አዝሎ መጓዝ በሰው ልጅ ውስጣዊ ማንነት ላይ ትልቅ ሸክም እንደሚሆንና ይቅርታ ግን ይህንን ሸክም በማቃለል መንፈሳዊና ስነ-ልቦናዊ ፈውስን እንደሚያመጣ አስረድተዋል።
ቀሲስ ፋሲል እንደገለጹት፣ በኅብረተሰባችን ዘንድ እንደ መስቀል፣ ጥምቀትና ፋሲካ ባሉ በዓላት ወቅት ሰዎች ለይቅርታ የሚነሳሱት በዓላቱ የመገናኛ፣ አብሮ የመብላትና የመጠጣት አጋጣሚዎች ስለሚፈጥሩ ነው።
ይህ ልማድ በተለይ በገጠር አካባቢዎች ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ ካለው የመገናኘት ባህል ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በሃይማኖታዊ መርህ ይቅርታ ጊዜ የማይወሰንለትና ዘወትር ሊተገበር የሚገባው ተግባር መሆኑን ቀሲስ ፋሲል በአጽንኦት ገልጸዋል።
ብዙውን ጊዜ ሰዎች ይቅርታ የምናደርገው ለበደለን ሰው ይመስላቸዋል ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ነገር ግን ይቅርታ በቅድሚያ ለራሳችን የምንሰጠው ትልቅ ስጦታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
“ቂም መያዝ ሌላውን ለመጉዳት መርዝ ራስን የመጠጣት ያህል ነው” የሚለውን የኔልሰን ማንዴላን አባባል በማንሳት፣ ቂም መያዝ አእምሮን ደጋግሞ ወደ ተጎዳበት ወቅት በመመለስ ለበሽታ እንደሚዳርግ አስረድተዋል።
ለይቅርታ ምንም አይነት ወሰን ሊቀመጥለት እንደማይገባ ባለሙያው ገልጸዋል። ይቅርታ ካለማድረግ የሚመጣ ቂም በደለኛውን ሰው በሩቅ ሆኖ ህይወታችንን እንዲቆጣጠር እድል እንደሚሰጠውም አክለዋል።
ይቅርታ ወቅት የለውም ያሉት የስነ ልቦና ባለሙያው በበአላት ወቅት ይሚደረገው ይቅርታ መልካም ቢሆንም ለዘለቴታ ሰላምና እረፍት ግን ይቅርታ የሁል ጊዜ ተግባር መሆን እንዳለበት መክሯል፡፡
ይህ ወቅት ለክርስትና እምነት ተከታዮች የጾምና የጸሎት ጊዜ መሆኑን ጠቁመዉ፤ ምዕመናንም ይቅርታ የፍቅር ተረድተዉ ፣ በዓላትን ሳይጠብቁ በየቀኑና በየሰዓቱ ይቅር የመባባል ልብ ሊኖራቸው እንደሚገባ ቀሲስ ፋሲል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በቶለሳ መብራቴ