AMN- ሚያዝያ 1/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ባለፉት 5 ዓመታት ከ2ሺ የሚበልጡ የተሸከርካሪ ማቆሚያ በከተማዋ መገንባታቸውንና ከ4ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ገለፀ።
ተቋሙ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በኮሪደር ልማት የለሙ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ጨምሮ የትራፊክ እንቅስቃሴውን የሚያሳልጡ 416 የመንገድ ዳር ፓርኪንጎችን ተረክቦ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ዲባባ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
182 የምድር ላይ /On Street Parking/ ፓርኪንጎች ስራ ላይ መዋላቸውንና፣ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ለሌላ ዓላማ የዋሉ የህንጻ ስር ፓርኪንጎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ 945 ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
461 ህንጻዎች ደግሞ በከፊል ለተሽከርካሪ ማቆሚያነት እንዲውሉ የማድረግ የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ወ/ሮ ገነት ገልፀዋል። የፓርኪንግ ቦታዎችን ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ አገልግሎቱን ከሰው ንኪኪ ነጻ በማድረግ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ተደርጓል፡፡

በፓርኪንግ ማስተዳደርና አገልግሎት መስጠትም 416 ማህበራት አንዲደራጁ በማድረግ ከ4ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ወጣቶቹ የፓርኪንግ የአገልግሎት ክፍያ እንዲቀበሉና በ70/30 መርህ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን አስተዳድረው ለመንግስትም ገቢ እንዲያስገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል በመንገዶች ዳርና ዳር ይቆሙ የነበሩ ተሸከርካሪዎች ከመንገድ በመውጣቸው በአራቱም አቅጣጫ ይደርስ የነበረው የትራፊክ መጨናነቅ በመቀነሱ አሁን ላይ በተነጻጻሪ የከተማዋ የትራንስፖርት ፍሰት የተሳለጠ መሆኑን ወ/ሮ ገነት ዲባባ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ገልፀዋል፡፡
በያለው ጌታነህ