የቻይናውያንን ልብ ያሞቀው የኢትዮጵያውያን የታማኝነት ጥግ

You are currently viewing የቻይናውያንን ልብ ያሞቀው የኢትዮጵያውያን የታማኝነት ጥግ
  • Post category:ባህል

AMN- ሚያዝያ 1 /2018 ዓ.ም

ከብር በላይ “ታማኝነት”፦ በብሔራዊ ሙዚየም የተገኘው የሥነ-ምግባር አርአያ!

ሶንግ ጆንግ የተባለ ቻይናዊ ጎብኝ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን የጥንት ታሪክና ባህል ለማየት የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ብሔራዊ ሙዚየም አመራ፡፡ ጉብኝታቸውን በደስታ አጠናቀው ከሙዚየሙ ቢወጡም፣ አንድ ትልቅ ነገር መዘንጋታቸውን ግን ልባቸው አላወቀም ነበር፡፡ 47 ሺህ ብር የኢትዮጵያ ብር የያዘ ቦርሳ!

በዚያው ሰዓት በሙዚየሙ የትኬት ሽያጭ መስኮት ላይ ወ/ሮ ጌራወርቅ አሰፋ በስራዋ ላይ ነበረች፡፡ ለሥራዋ ካላት ጥልቅ ፍቅር ባሻገር፣ የደንበኞችን ደህንነት መጠበቅ የቀዳሚነት ተግባሯ ነው፡፡

በድንገት ያንን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ስትመለከት፣ ቅንጣት ታህል ሳታመነታና የራስዋን ጥቅም ሳታስቀድም፣ ጉዳዩን ለባልደረቦቿ ጭምር ገልፃ ብሩን በጥንቃቄ ጠብቃ ማቆየትን መረጠች፡፡

ከአራት ሰዓታት ረጅም ጥበቃ በኋላ፣ ሶንግ ጆንግ የጠፋበትን ገንዘብ አስታውሶ በድንጋጤና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ወደ ሙዚየሙ ተመለሰ፡፡ “ገንዘቤን አገኝ ይሆን?” እያለ በጥርጣሬ ቢመጣም፣ የጠበቀው ግን ከጠበቀው በላይ ነበር፡፡ የታማኟ ባለሙያ እጅ የጠፋውን ገንዘብ አንድም ሳንቲም ሳይጎድል አስረከበችው!

በወቅቱ ብሩን ሳስረክበው ከሱ በላይ ደስተኛ ነበርኩ: ትልቅ ሸክም የተገላገልኩ ያክል እፎይታ ተሰምቶኛል ስትል ወ/ሮ ጌራወርቅ ለኤኤምኤን ዲጂታል ሚዲያ ተናግራለች፡፡ በኢትዮጵያውያን ቅንነት ልቡ የተነካው ሶንግ ጆንግ፣ ያን የማይረሳ ቀን በራሱ የእጅ ጽሁፍ አድናቆቱን እና የወ/ሮ ጌራወርቅን ታማኝነት አስፍሮታል፡፡

ይህ አጋጣሚ ለሁላችንም፣ በተለይም በአገልግሎት ዘርፍ ላለን ባለሙያዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ምክንያቱም በእኔ ውስጥ ሃገሬ አለች; ተቋሜ የሃገር ምልክት ነው ስትል ወ/ሮ ጌራ ወርቅ ገልፃለች፡፡

“ታማኝነት የሀገር ገጽታ ነው!” ወ/ሮ ጌራወርቅ ያሳየችው ይህ ድርጊት የእሷን ማንነት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍና የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት በዓለም ፊት ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ስራ አስፈፃሚ፣ ለዚህች የሥነ-ምግባር አርአያ የምስጋና ደብዳቤ በማበርከት እውቅና እንደሰጣትና በዚህም ደስተኛ መሆናን ተናግራለች።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review