ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ቶሎ የተሰኘ የክፍያ ስርዓትን በቴሌ ብር አስጀመረ

You are currently viewing ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ቶሎ የተሰኘ የክፍያ ስርዓትን በቴሌ ብር አስጀመረ

AMN- ሚያዚያ 01/2018 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ቶሎ የሚል ስያሜ የተሰጠው የፍጥነት መንገድ የክፍያ ስርዓትን በቴሌ ብር አስጀመረ።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ፣ የክፍያ መንገዶችን በቴክኖሎጂ ማገዝ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልፀዋል።

ቶሎ የተሰኘው ፈጣን የዲጂታል የክፍያ አማራጭ በፍጥነት መንገዶች ለሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ቀላልና ምቹ የክፍያ ስርአት እንደሆነም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል ፣ የፈጣን መንገድ የክፍያ ስርዓት እስካሁን በተለምዶ የእጅ በእጅ አከፋፈል ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰው ቶሎ የተሰው የክፍያ ስርዓት እንደ ስያሜው ፈጣንና ቀልጣፋ የአከፋፈል ስርዓትን እውን የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ቶሎ ለመንገደኞች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው “ቶል ኦንላይን ሊንክድ ኦፕሽን” (Tall Online Linked Option ) የሚል መጠሪያ ያለው አዲሱ ቴክኖሎጂ ቶሎ ከሚለው የአማርኛው ትርጉም ጋር የተመሳሰለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቶሎ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለመጠቀም አሽከርካሪዎች አስቀድመው ከክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር ለደንበኝነት የሚያበቃቸውን ቅጾች በኦንላይን በመሙላት አር ኤፍ ኪው አር ኮድ ያለው አነስተኛ ወረቀት በአካል ተገኝተው መውሰድና ወዲያውኑ በመኪናቸው ለካሜራ እይታ ምቹ በሆነ የፊት ለፊት መስተዋት ላይ በቋሚነት መለጠፍ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

በአዲስ አዳማ ፣ በድሬዳዋ ደወሌ እና በሞጆ ሃዋሳ የፍጥነት መንገዶች በቀን ከ32 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች እንደሚጠቀሙ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት ማስጀመሪያው ላይ ተጠቅሷል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review