ከለውጡ ወዲህ በመዲናዋ ማዕድ ማጋራትና መደጋገፍ ባህል ሆኗል

You are currently viewing ከለውጡ ወዲህ በመዲናዋ ማዕድ ማጋራትና መደጋገፍ ባህል ሆኗል

AMN- ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በከተማዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፣ አረጋውያንና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡

አስተዳደሩ ባዘጋጀው በዚህ የበዓል መርሃ ግብር በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ከ233 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

መርሃ ግብሩ “ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት” መርህን መሰረት በማድረግ ሁሉም ዜጋ በዓሉን ያለምንም የኢኮኖሚ ጫና በደስታ እንዲያሳልፍ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የማዕድ ማጋራት ተግባር ከለውጡ ወዲህ በከተማዋ እንደ ባህል የዳበረ ሲሆን ፣ የዘንድሮውም መርሃ ግብር የከተማዋ አስተዳደር ከህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በመተባበር አከናውኗል፡፡

የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ ፣ መርሃ ግብሩ ድህነትን በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርና በመረዳዳት የምናሸንፍበት ነው ብለዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ ብቻ ሳትሆን የርህራሄና የሰብአዊነት ተምሳሌት እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕድ ማጋራቱ ተጠቃሚ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የቀረበው ድጋፍ በዓሉን ያለ ስጋትና በደስታ እንዲያሳልፉ ትልቅ እገዛ እንዳደረገላቸውም ገልጸዋል።

ይህ ተግባር በችግር ጊዜ አብሮ መቆምን፣ በደስታ ጊዜ መጋራትን እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ያሳየ መርሃ ግብር ሆኖ ዘልቋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review