የትንሳኤ በዓል ሲታሰብ ቀዳሚው ምስል የታሸገው መቃብር መከፈትና ትልቁ ድንጋይ ተንከባሎ መገኘቱ ነው። ይሁን እንጂ ከሃይማኖታዊው ሥነ-ስርዓት ባሻገር፣ ትንሳኤ ለሰው ልጅ ልቦና ትልቅ ትርጉም አለው፤ ይኸውም ይቅርታ ነው። በዓሉ የሞት ድል መነሳት ብቻ ሳይሆን፣ በጥላቻና በቂም የጠቆረ ማንነት ዳግም የሚታደስበት፣ የልብ ድንጋዮች የሚንከባለሉበት ታላቅ የይቅርታ አደባባይ ነው።
በሥነ-ልቦናው ዓለም ቂም እንደ ታሸገ መቃብር ነው። ሰው በበደሉት ሰዎች ላይ ቁጣንና በቀልን አፍኖ በያዘ ቁጥር፣ ራሱን በጨለማ ክፍል ውስጥ እንደዘጋ እስረኛ ይቆጠራል። ትንሳኤ ግን ይህንን ጨለማ ጥሶ የሚወጣ ብርሃን ነው።
በዕለተ ትንሳኤ ወደ መቃብሩ የሄዱት ሴቶች ትልቁ ጭንቀታቸው “ድንጋዩን ማን ያንከባለልልናል?” የሚል ነበር። በሰው ልጅ ማህበራዊ ህይወት ውስጥም ለዓመታት የቆዩ ቂሞች፣ ያልተፈቱ አለመግባባቶች እና የቤተሰብ መቃቃሮች እንደ ከባድ ድንጋይ ልባችንን ይጫኑታል።
በዓሉ ሲመጣ “እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ” የምንባባለው ለቁሳዊው ብርሃን ብቻ አይደለም። ይልቁንም በልባችን ላይ የከበደውን የጥላቻ ድንጋይ አንከባልለን እንድንጥል፣ ለዓመታት ካልተነጋገሩት ጎረቤት ጋር ሰላም እንድንል፣ በጸጸት የታሰረውን ማንነታችንን ፈትተን ራሳችንን ይቅር እንድንል ጥሪ ያደርጋል።
የትንሳኤ በዓል ከይቅርታ ጋር ያለው ቁርኝት የሚጀምረው “ከመስቀሉ ስር” ነው። በክርስትና አስተምህሮ፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ማለቱ፣ ይቅርታ በምላሽ ላይ ሳይሆን በልግስና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያሳያል። ትንሳኤ ይህ የይቅርታ ጉዞ ፍጻሜውን ያገኘበት፣ ህይወት በሞት ላይ፣ ፍቅር በጥላቻ ላይ ድል የተቀዳጀበት ዕለት ነው።
በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ውስጥ ይቅርታ የሰው ልጅ ሊያሳያቸው ከሚችላቸው ታላላቅ የሥነ-ምግባር እሴቶች አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል። አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ይቅርታን እንደ ግዴታ ወይም እንደ ቅድስና መንገድ ያዩታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ይቅርታ እስከምን ድረስ መሆን አለበት? በሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና ሥነ ልቦና ረገድ ምን መልክ አለው?
በብዙ የእምነት ሥርዓቶች ውስጥ ይቅርታ ቁጥር ወይም ገደብ ሊኖረው እንደማይገባ ይታመናል። በክርስትና አስተምህሮ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ “እስከ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመለሰለት “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት” (ማለትም ማለቂያ የሌለው) በሚል ነበር። ይህም ይቅርታን በቁጥር መገደብ እንደሌለብን ያሳያል።
ይቅርታ ለሌላው ሰው ብቻ የሚደረግ ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለውን ቁጣ፣ ቂም እና ጥላቻ የምናስወግድበት መንገድ ነው። በኢስላም አስተምህሮ ይቅር ባይነት የአላህ (ሱ.ወ) ባህሪ እንደሆነና ሰዎችን ይቅር የሚል ሰው ከአላህ ዘንድ ትልቅ ምንዳ እንደሚያገኝ ይገለጻል። ይቅርታ ማድረግ ሰላምን ለሚሰጥ ሰው የውስጥ ነጻነትን ያጎናጽፋል።
ይቅርታ ማለት የበደሉን ሰው ድርጊት መደገፍ ወይም በደሉን መርሳት ማለት አይደለም። ይልቁንም በደሉን አምኖ መቀበል፣ ነገር ግን አጸፋ ላለመመለስ መወሰን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በብዙ አስተምህሮዎች ይቅርታ ከፍትህ ጋር አብሮ ይሄዳል። ይቅር ማለት የበደለውን ሰው ከህግ ተጠያቂነት ማዳን ባይሆንም፣ በግል ደረጃ ግን ከቂም መፈታትን ያመለክታል።

በቀበና መድያነዓለም ሰባኪ ወንገልና ቤተሰብ አማካሪ መጋቢ ኤልያስ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ ሰው ከፈጣሪው ምሕረትን ለማግኘት መጀመሪያ እርሱ ሰዎችን ይቅር ማለት እንዳለበት ይነገራሉ። “እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል…” የሚለው ጸሎትም የሚያሳየው፣ የእኛ ይቅር ባይነት ለፈጣሪ ምሕረት በር መክፈቻ መሆኑን ነው።
ይቅርታው እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት ለሚለው ጠላትን እስከ መውደድ የሚለው ነው፡፡ እጅግ አስቸጋሪው ነገር ግን በሃይማኖታዊ ደረጃ የሚጠበቀው ከፍተኛው እርከን የጎዱንን ሰዎች ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን፣ መልካም እንዲሆንላቸው መመኘትና መጸለይ ነው ሲሉ መጋቢ ኤልያስ ቀሲስ ፋሲል የሚገልጹት።
እንዲሁም ይቅርታ ለራስ ሰላም መስጠት ነው፡፡ ይቅርታን እስከ መጨረሻው ማድረግ ያለብን የራሳችን መንፈሳዊ ጉዞ እንዳይገታና በቂም ድንጋይ እንዳንታሰር ነው።
መጋቢ ኤልያስ ቀሲስ ፋሲል እንደሚገለጹት፤ ይቅርታ መስፈርት የሌለው፣ ገደብ የሌለው እና የልብን ቅንነት የሚጠይቅ ተግባር ነው። ይቅርታ ስናደርግ ሰውን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንንም ነጻ እናወጣለን።
በሥነ-ልቦና እይታ፣ ይቅርታ ከሃይማኖታዊው ትርጓሜ በተለየ መልኩ ለራስ አእምሮአዊ ጤና እና ሰላም ሲባል የሚደረግ የውስጥ ውሳኔ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ይቅርታ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት ለሚለው ነጥብ ሥነ-ልቦና የሚከተሉትን መስፈርቶች ያስቀምጣል፡፡
በሥነ-ልቦና ረገድ ይቅርታ ማለት የበደለንን ሰው “ነጻ ማውጣት” ሳይሆን፣ ራሳችንን ከቂም፣ ከቁጣና ከጭንቀት ሰንሰለት መፍታት ማለት ነው። ስለዚህ ይቅርታው እስከ መጨረሻው መሆን ያለበት የበደለን ሰው ድርጊት በእኛ ስሜት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን እስከሚያቆም ድረስ ነው።
በሥነ-ልቦና ረገድ ይቅርታ በውስጣችን ያለውን ጥላቻ ማጠብ ነው። ይሄ በማንኛውም ሁኔታ ሊደረግ ይችላል። መታረቅ ደግሞ ግንኙነቱን እንደነበረ መቀጠል ነው። ይቅርታ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት? በደሉን ይቅር እስከማለት ድረስ! ነገር ግን ግንኙነቱን መቀጠል ለደህንነታችን አስጊ ከሆነ (ለምሳሌ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ጥቃት ካለ) መራቅን እንደ አማራጭ ያስቀምጣል።

ይቅርታ ማድረግ ማለት ሌላው ሰው በድጋሚ እንዲጎዳን መፍቀድ ማለት አይደለም። “ይቅር ብዬሃለሁ፣ ነገር ግን በድጋሚ እንድትጎዳኝ አልፈቅድም” የሚል ጠንካራ ድንበር ሊኖረን ይገባል። ይቅርታው ድንበር እስከማበጀት ድረስ መሄድ አለበት፤ ያለበለዚያ ይቅርታው ወደ “ራስን ማስበደል” ሊቀየር ይችላል።
በሥነ-ልቦና (Psychology) ሳይንስ ይቅርታ ማለት የበደለንን ሰው ድርጊት መፍቀድ ወይም መርሳት ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለውን አሉታዊ ስሜት ሆን ብለን የምንተውበት የውስጥ ለውጥ ሂደት ነው።
ይቅርታ እስከ ምን ድረስ መሆን እንዳለበት በዘርፉ የታወቁ እንደ ሮበርት ኤንራይት እና ኤቬርት ዎርቲንግተን ያሉ የስነ ልቦና ምሁራን ምልከታቸውን እንደሚከተለው አስቀጧል፡፡
የይቅርታ ሥነ-ልቦና አባት ተብለው የሚታወቁት ዶ/ር ሮበርት ኤንራይት፣ ይቅርታ “ምንም ቅድመ ሁኔታ የሌለው” መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ። እንደ እሳቸው እይታ በደለኛው ባይጸጸትም እንኳ ይቅርታ በሌላው ሰው ንስሐ ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ሌላው ሰው ይቅርታ ካልጠየቀ እኛ በቂም ታስረን እንቀራለን። ይቅርታው እስከ መጨረሻው ደርሷል የሚባለው፣ ለበደለን ሰው በክፉ ምትክ መልካምን የመመኘት ደረጃ ላይ ስንደርስ ነው።

ዶ/ር ዎርቲንግተን በይቅርታ እና በጤና መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠኑ ምሁር ናቸው። እሳቸው ይቅርታ በሁለት ይከፈላል ይላሉ፡፡ የውሳኔ ይቅርታ እና የስሜት ይቅርታ በማለት፡፡
የውሳኔ ይቅርታ በቀልን ለመተው መወሰን ሲሆን የስሜት ይቅርታ ደግሞ በውስጥ ያለውን የፍርሃትና የቁጣ ስሜት በአዎንታዊ ስሜቶች መተካት እንደሆነ በ (Forgiveness and Reconciliation) መጽሃፋቸው በስፋት ያነሳሉ።
የሥነ-ልቦና ትንተና (Psychoanalysis) አባት ሲግመንድ ፍሮይድ እንደሚለው፣ ያልተፈቱ ቂሞች በሰው ልጅ ንቃተ-ህሊና ውስጥ ተቀብረው የስብዕና መዛባት ያመጣሉ የላል። ይቅርታ ራስን ነጻ እስከ ማውጣት ድረስ መድረስ አለበት። እራሳችንን ለበደልነው በደል ወይም ለፈቀድነው ስህተት ራሳችንን ይቅር እስክንል ድረስ ሂደቱ መቀጠል አለበት።
በቶለሳ መብራቴ