AMN ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም
በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ በሚገኘው 2ኛው የአፍሪካ የከተሞች ፎረም ላይ፣ በአዳዲስ ፈጠራዎችና ስልቶች የታጀበው “የአዲስ አበባ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ሞዴል” ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ተሞክሮ ሆኖ ቀረበ።
ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በሚቆየው በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ፣ አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ተጨባጭ የለውጥ ውጤቶች በዝርዝር ቀርበዋል። በተለይም ከተማዋ በከተማ አመራር ሥርዓት፣ በአዳጊና ተከታታይ የገቢ አሰባሰብ፣ እንዲሁም ውጤታማ በሆነ የፕሮጀክቶች ፋይናንሲንግ ረገድ ያገኘቻቸው ስኬቶች በፎረሙ ተሳታፊዎች ትኩረት አግኝተዋል።
በተጨማሪም የከተማዋን ገጽታ የቀየሩት የወንዞችና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው የቀዳማይ ልጅነት (Early Childhood Development) ፕሮጀክቶች አፈጻጸም “የአዲስ አበባ አዲሱ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ሞዴል” ተብለው ተቀምረው ለቀሩት የአፍሪካ ከተሞች በልምድ ተምሳሌትነት ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ በፎረሙ ላይ እንደገለጸው፣ አዲስ አበባ ተሞክሮዋን ለሌሎች ከማካፈል ባለፈ፣ በከተማዋ የተጀመረውን ፈጣን ዕድገት ይበልጥ ለማስቀጠል የሚያግዙ አዳዲስ ልምዶችንም እየቀሰመች ይገኛል። በዚህም በተለይ በቤት አቅርቦትና ፋይናንሲንግ እንዲሁም በከተማ ቱሪዝም መዳረሻዎች አስተዳደር ዙሪያ ከሌሎች አገራት ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ማግኘት መቻሉ ታውቋል።
ይህ መድረክ አዲስ አበባ በአህጉሪቱ ያላትን የዲፕሎማሲያዊና የከተማ ልማት ሚና ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል – የከንቲባ ጽ/ቤት