AMN- ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት በቪዬና በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኢነርጂ እና አየር ንብረት ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
አፍሪካ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኢነርጂ እምቅ አቅም በመጠቀም እና በወሳኝ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ወደ ኢንዱስትሪያል እድገት ለመሸጋገር ያላትን ልዩ እድል አጉልተው ገልጸዋል።
የኢነርጂ ተደራሽነት ውስንነት፣ የመሠረተ ልማት ክፍተቶች እና የገበያ ተደራሽነት እጥረትን ጨምሮ ያሉ እንቅፋቶችን መፍታት አጣዳፊ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራች መሆኗን እና ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት ከ95 በመቶ በላይ ንፁህ ኃይል የማመንጨት ተግባር እየከወነች ነው ብለዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኦኮኖሚ ልማት ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ከፎረሙ ጎን ለጎን ከደቡብ ሱዳን እና ኦስትሪያ አቻወቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማካሄዳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።