AMN ሚያዝያ 2/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ዓለም የሚያደንቃቸው ብርቅዬ አትሌቶችን ማፍራት የቻለች ቢሆንም፣ ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የሚያስችሉና ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማቶች ግን እጥረት ነበረባት።
ይህ በስፖርት ዘርፉ የነበረው የመሰረተ ልማት ክፍተት፤ እንደ ቁጭት ብቻ ሳይታይ የዘርፉን አገራዊና ትውልዳዊ ፋይዳ በውል በመረዳት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆኖ ምላሽ እያገኘ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ለነዋሪዎች እንቅስቃሴና ጤና ምቹ የሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከማስፋፋት ባለፈ፣ ከሌሎች የልማት ስራዎች ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እውን ሆነዋል።
በከተማችን በፍጥነትና በጥራት የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ መሰረተ ልማቶች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል። ዛሬ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን ለማካሄድ ዋነኛ የስበት ማዕከል መሆን ችላለች።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ማሳያ የፊታችን ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አለም አቀፍ ስታዲየም የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የ “Addis Ababa Grand Prix” የአትሌቲክስ ውድድር ነው። ይህ ውድድር አብዛኛው የዓለም ሕዝብ በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ የሚያውቃቸውን እጅግ ውጤታማና ዝነኛ አትሌቶች ወደ መዲናችን ያመጣል።
በቅርብ ዓመታት በተመዘገበው አስደናቂ የስፖርት መሰረተ ልማት ለውጥ ምክንያት ዕውን የሆነው ይህ ውድድር፣ ሀገራችን በስፖርቱ ዘርፍ ያላትን ተጽዕኖ ይበልጥ ከማሳደጉም በላይ ዓለም የአዲስ አበባን ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲረዳ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል።
በእርግጥም በከተማችን ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የስፖርት መሰረተ ልማቶች በቀጣይም ለአዲስ አበባ ተጨማሪ የስበት ማዕከላት ናቸው።- የከንቲባ ጽ/ቤት