AMN – ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል በመስቀል ላይ ያሳለፈውን መከራ የተቀበለበት ዕለተ መታሰቢያ የሆነው ስቅለት፣ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት እየታሰበ ይገኛል።
ምእመናን የክርስቶስን መከራ በማሰብ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ዕለቱን እያሳለፉ ነው።
በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የስብከተ ወንጌል ኃላፊ መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ እንደገለጹት፣ ዕለቱ የሰው ልጅ ከኃጢአት ባርነት ነጻ የወጣበት ታላቅ የድኅነት ቀን ነው።
የስቅለት ዕለት የሚከናወኑ ሥነ ሥርዓቶች ከሌሎች ቀናት በተለየ መልኩ እጅግ ጥብቅና በሱባኤ የተሞሉ ናቸው።
በርካታ ምእመናን ከጸሎተ ሐሙስ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ እኩለ ሌሊት ድረስ የሚቆይ ጾም በመያዝ በቤተክርስቲያን ቅጽር ተገኝተው የክርስቶስን መከራ እያሰቡ በመስገድ ንስሐ ይገባሉ።

ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸውን ሰባቱን አባባላት ለምእመናን በንባብ ያሰማሉ።
መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ አክለው እንደገለጹት፣ በዕለቱ የሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ለሰቀሉት ሰዎች ያደረገውን ጸሎትና ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው።
ይህም ምእመናን ይቅርታንና ፍቅርን ከእየሱስ ክርስቶስ እንዲማሩ የሚያደርግ የሥነ-ሥርዓቱ ዋነኛ አካል ነው።
በአሁኑ ሰዓት ምእመናን በጸሎት ሆነው የጾሙን መጠናቀቅና የትንሣኤን ብርሃን በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
በበረከት ጌታቸው