የትንሣኤ በዓል ገበያን ለማረጋጋት በትላልቅ የገበያ ማዕከላት ምርት በቅናሽ ዋጋ እየቀረበ ነዉ

You are currently viewing የትንሣኤ በዓል ገበያን ለማረጋጋት በትላልቅ የገበያ ማዕከላት ምርት በቅናሽ ዋጋ እየቀረበ ነዉ

AMN ሚያዝያ 2/2018

የትንሣኤ በዓል ገበያን ለማረጋጋት በትላልቅ የገበያ ማዕከላት ምርት በቅናሽ እየቀረበ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል በመገኘት የበዓል ገበያ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል። በላፍቶ ሁለገብ ገበያ ማዕከል ሽንኩርት በኪሎ ከ25 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

​ምክትል ከንቲባው በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት በገበያ ማዕከሉ የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዲገቡ ቀደም ብሎ በተሰራው ዝግጅት መሠረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይም በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ድንች ያሉ ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።

​ይህም ገበያውን ለማረጋጋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። በላፍቶ ገበያ ማዕከል የሽንኩርት ምርት እንደየደረጃዉ ከ25 ብር ጀምሮ እስከ 50 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ይህም ማዕከሉ ምርትን በጅምላ ተረክቦ ወደ ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ለማሰራጨት ያለውን ዝግጁነት ያሳያል።

ወቅታዊ ሁኔታዎችን ሰበብ በማድረግ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ ለመፍጠር ገበያ የተረጋጋ እንዳልሆነ አሉባልታ ለመንዛት የሚሞክሩ መኖራቸውን በመግለፅ ነጋዴዎችም ሆነ ሸማቹ ማህበረሰብ ወደ ላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል መጥቶ መግዛት እንደሚችል አሳስበዋል።

​አልፎ አልፎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአቅርቦት ችግሮችንና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመለየት የከተማ አስተዳደሩ ጥብቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል የሚገኙ ነጋዴዎች በበኩላቸው የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ምርት በስፋት እንዲገባ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ሰሞኑን ያለአግባብ ዋጋው ጨምሮ የነበረው የሽንኩርት ምርት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ እንዳሳየ ተናግረዋል።

​ነጋዴዎቹ አክለውም በማዕከሉ ያለው የምርት አቅርቦትና ክምችት ከአዲስ አበባ ፍላጎት አልፎ ለክልሎች የሚተርፍ መሆኑን መግለጻቸዉን ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review