AMN – ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም
የስቅለት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጥልቅ ትርጉም ያለውና የሰው ልጅ ድኀነት የታወጀበት ታላቅ ቀን መሆኑን ሀይማኖታዊ አስተምሮው ያስረዳል።
ይህ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተበትን ዕለት ታስቦበት የሚውልበት ነው።
በቦሌ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤልና ጻድቁ አቡነ ጎርጎሪዮስ ቤተክርስቲያን ሰብከተ ወንጌል ሀላፊ መጋቢ ሀዲስ ለይኩን ብርሀኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስቅለት ዕለት ከሌሎች በዓላት በተለየ መልኩ በታላቅ ኀዘን፣ በጾም እና በጸሎት ሲታሰብ ይውላል ብለዋል ።

ምዕመናን ከጠዋት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ በቤተክርስቲያን በመገኘት አእላፍ ስግደቶችን ይሰግዳሉ።
ይህ ስግደት ክርስቶስ ለሰው ልጆች የተቀበለውን መከራ ለማሰብና ለሰራነው ኃጢአት ይቅርታን ለመጠየቅ የሚደረግ ነው በመሆኑም ከመስቀሉ ፍቅር፣ ትህትና እና ትእግስትን በመማር ማክበር ይገባል ብለዋል ።
ሙሉ ለሙሉ ከጌታ መያዝ ጀምሮ እስከ መቃብር መውረዱ ድረስ ያለውን መከራ የሚዘክሩ መጻሕፍትና የወንጌል ክፍሎች በየሰዓቱ ይነበባሉ።
በቤተልሔም አየነው