የትንሣኤ በዓልን ስናከብርየተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ይሁን ሲሉየኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

You are currently viewing የትንሣኤ በዓልን ስናከብርየተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ይሁን ሲሉየኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

የትንሣኤ በዓልን ስናከብር ካለን ከፍለን የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣትና የታረዙትን በማልበስ የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ሲሉ የኃይማኖት አባቶች መንፈሳዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዘንድሮውን የትንሣኤ በዓል አስመልክቶ የኃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ በዓለ ትንሣኤ የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጫ እና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን በመገንዘብ፣ በዓሉን ስናከብር ካለን ከፍለን የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣትና የታረዙትን በማልበስ የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት ነው።

በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የትንሣኤ በዓላችንን ስናከብር ዓለም በክፋቷ ላጨለመባቸው ወገኖች ካለን ከፍለን የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ ቀኑ ለሁላችንም ፍጹም ብርሃን ሆኖ ይውል ዘንድ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ብለዋል።

ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱና ከመነሳቱ በፊት ለቅዱሳን ሐዋርያት በተደጋጋሚ አስረድቷቸዋል፤ ስለሆነም ሞትና ትንሣኤው ድንገተኛና የግድ ሳይሆን ታውቆ ያደረገው ውድ እንደሆነ ከዚህ እውነታ እንረዳለን ብለዋል።

የሰውን ምልአተ ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ሰርዞ ሰውን ከሞት ቅጣት ነጻ ለማውጣት ብቃት ያለው ቤዛዊ መስዋዕት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነበረበት፤ ይሁን እንጂ ከዚህ ዓይነት ቤዛዊ መስዋዕት ብቁ የሆነ ከፍጡራን ወገን ስላልተገኘ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት፣ ራሱ ተቀባይ መስዋዕት አምላክ ሆኖ የቤዛነታችንን መስዋዕት ራሱ በራሱ ለራሱ አቀረበ።

በዚህ ቤዛዊ መስዋዕትነትም እኛን ከሞት ቅጣት ነጻ አደረገን፤ ትንሣኤያችንንም በትንሣኤው አበሰረ፤ በክርስትና ኃይማኖት የሚገኝ ፍጹም ድኅነትና ነጻነት በዚህ ቤዛዊ መስዋዕት ላይ የተመሠረተ ነው። ጌታችን በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ሊያበስረን የትንሣኤ ሰዎች ሆነን በመንፈስና በሞራል በማደግ ብርሃናተ ዓለም ልንሆን እንጂ እንደገና የጨለማው ኃይል መሣሪያዎች ልንሆን አይደለም ብለዋል።

ዓለም እንደ አጠቃላይ በጨለማ ተውጣ ስትተረማመስ የሚታየው ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ምርጫዋ ስላደረገች መሆኑን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ ስለሆነም የእኛ ምርጫ ብርሃን የሆነው እግዚአብሔር እንዲሆን የቤተ ክርስቲያን ዘወትር ጥሪ ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፣ “ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማስቀደም፣ “በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው እግዚአብሔር ከሁሉ አስቀድሞ የተግባርና የተሞክሮ አምላክ መሆኑን ነው። ይህ ተሞክሮ ደግሞ በልጁ ሥጋ መልበስ ፍጹምነትን አግኝቷል። የክርስቶስ የትንሣኤውም ምስጢር አንድን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላውን የሰው ልጅ ሕይወት እንደሚመለከት የምንረዳው በወንጌልና በትንሣኤ የምሥራች ነው” ብለዋል።

በዚህ ቀን ብዙ ነገሮች ተከናውነዋል። በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ኃጢአትና ሞት ድል ተነስተዋል። የመጀመሪያው አሮጌው በኃጢአት የተበከለው ፍጥረት ፍጻሜውን አግኝቶ አዲስ ፍጥረት በክርስቶስ ተጀምሯል። እኛም በዚህ በፋሲካ ቀን አዲሱን የዓለም የመጀመሪያ ቀን እናስታውሳለን። የመጨረሻውንም ቀን በተስፋ እንጠባበቃለን። ይኸውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር የሚመጣበት ቀን ነው ብለዋል ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል፡፡

ትንሣኤን የሚያምኑ ልጆች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችን ደስታንና ተስፋን ያዘለ እንዲሆን ተጠርተናል። በምናደርገው በሕይወታችን ሁሉ የአምላክ ቃል መቃኛችን ሊሆን ይገባል። የአምላክን ቃል የሚቋቋም፣ ቅዱስ መንፈሱን የሚያሳዝን፣ ከክርስትና ሕይወት ያልተስማማ ጥላቻን፣ መለያየትንና መገዳደልን ሁሉ እናስወግድ። በእውነት ፈጣሪያችንንም እንደምንወድ በቃላችንና በሥራችን እናሳይ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

አክለውም፣ በቤታችንም ሆነ በአገራችን የሚገዛን ጌታ አድርገን እንሹመው። ወደ እርሱ በመቅረብ በጽድቅ ሕይወት በመጽናት፣ በሕይወታችን መልካም ምግባርን እናሳይ። ከመላው የአገራችን ሕዝቦች ጋር በመተባበርና በአንድነት እንቁም። በዓሉንም ስናከብር እርስ በርሳችንም ይቅር በመባባል እንደተለመደው ከችግረኞች፣ አስታዋሽ ከሌላቸው፣ በጎዳናና በየመጠለያ ቦታዎች ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በማገዝና በመርዳት መሆን አለበት ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዓለ ትንሣኤው በአገራችን የተፈጥሮ ጉዳት ላጋጠማቸው መጽናናትን፣ በአገራችንና በመካከለኛው ምስራቅ ባሉት አገሮች የሚካሄዱት ጦርነቶች እንዲቆሙና ሰላም እንዲወርድ፣ ለታመሙት ምሕረትን፣ ላዘኑት መጽናናትን፣ በችግርና በጭንቀት ላይ ላሉ በጌታ መጎብኘትን፣ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው መመለስን፣ ለተራቡና ለተጠሙ ምግብና ውሃን እንዲሰጥልን፣ የተራራቁትን እንዲያቀራርብልን፣ በአጠቃላይ የትንሣኤው ፍሬ ፍቅርንና ወዳጅነትን፣ ትዕግስትና ትሕትናን የምናሳይበት ያድርግልንም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀንበሩ የትንሣኤውን በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፤ የትንሣኤውን መታሰቢያ በዓል ስናከብር በክርስቶስ ኢየሱስ መከራና ሰቆቃ፣ ሞትና ትንሣኤ ያገኘነውን የዘላለም ሕይወት እንዲሁም እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ በኩል የገለጸውን ወደር የሌለውን ፍቅሩን እያሰብን፣ ዕለቱን እግዚአብሔርን በተሰበረ ልብ በማምለክ እና በማመስገን ማሳለፍ ይኖርብናል ብለዋል።

አክለውም፣ ትንሣኤ ጥላቻ በፍቅር፣ መለያየት በአንድነት፣ ሐዘን በደስታ፣ እንዲሁም ሽንፈት በድል የተደመደመበት ስለሆነ በእኛም መካከል ጎልቶ መታየት ያለበት ፍቅር፣ ሰላም እና ይቅር ባይነት ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ይህም በፍጹም ቅንነት፣ መከባበርና መደማመጥ እንዲሁም በእርቅ የአገራችንን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እና የሕዝባችንን አንድነት በጽኑ አለት ላይ ለማቆም ያስችለናል ያሉት የካውንስሉ ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ፤ በመካከላችን አሉ የሚባሉ ልዩነቶችን በማስተዋልና በጥበብ ለመፍታት፣ ብሎም የበደልናቸውን ብቻ ሳይሆን የበደሉንንም በይቅርታ ለመቀበልና እውነተኛ ሰላም ለማስፈን ብንሠራ ጥላቻ እየደበዘዘ ፍቅር ግን እየጎለበተ ይሄዳልም ብለዋል።

እግዚአብሔር በቃሉ፣ “‘ለድሀ ቸር የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል’ ስለሚል የክርስቶስን ትንሣኤ ስናከብር በመካከላችን በልዩ ልዩ ችግሮች ውስጥ ያሉትን ወገኖቻችን በማሰብ፣ እነርሱም ከእኛ ጋር የደስታችን ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ከፍቅር የመነጨ ልግስና እንድናደርግላቸው ይገባል” ሲሉ አክለዋል።

አያይዘውም፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በጋሞ ዞን አንዳንድ ደጋማ ስፍራዎች በተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ እንዲሁም የመሬት መንሸራተት 125 ወገኖቻችንን በሞት ያጣን እና በብዙዎችም ላይ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አሁንም ተፈናቅሎ በመጠለያ ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ ሕዝባችን በታላቅ ሐዘን ውስጥ ስለሚገኝ በዚህ ወሳኝ ወቅት ስጦታችንን በተደራጀ ሁኔታ በማሰባሰብ የሐዘናቸው ተካፋይ መሆናችንን በተግባር እንግለጽ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘም የኃይማኖት አባቶች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ምርጫው የዜግነት መብት መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም በንቃት መሳተፍና ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሃይላይት፦ “ትንሣኤ ጥላቻ በፍቅር፣ መለያየት በአንድነት፣ ሐዘን በደስታ፣ እንዲሁም ሽንፈት በድል የተደመደመበት ስለሆነ፣ በእኛም መካከል ጎልቶ መታየት ያለበት ፍቅር፣ ሰላም እና ይቅር ባይነት ነው።”

በጋዜጣው አዘጋጆች

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review