ትስስርን ያጠበቁ እጆች

You are currently viewing ትስስርን ያጠበቁ እጆች

“በሁሉም በዓላት የምናደርገው የማዕድ ማጋራት ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የምንገልፅበት ተግባር ነው”


የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

በዓል ማለት ለራስ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት መቁረስ፣ ለራስ ማብሰል ብቻ ሳይሆን አቅመ ደካሞችን ማሰብ መሆኑን ‘የማዕድ ማጋራት’ ንቅናቄ በተግባር እያሳየን ይገኛል። ከመንግስት ቢሮዎች እስከ የሰፈር ወጣቶች የተዘረጋው ይህ የበጎነት እጅ የአዲስ አበባን ማህበራዊ የትስስር ገመድ በእጅጉ አጥብቆታል።

በበዓላት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የአንድነት ድባብ ከተማዋን ለየት ያለ ገጽታ ያላብሳታል። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተለመደ የመጣው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር፣ የአዲስ አበባን የቆየ የመረዳዳት ባህል ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ክስተት ሆኗል።

የትንሣኤ በዓልን መነሻ በማድረግ ማንሳት በወደድነው በዚህ ጉዳይ ላይ በበዓል ወቅት አቅመ ደካሞችን ለመርዳት በመንግስትና በግለሰቦች የሚደረገው የማዕድ ማጋራት ሥራ ፋይዳው ምንድን ነው? ማህበራዊ ግንኙነታችን እንዲጠናከር ምን ያህል ያግዛል? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን እንዳስሳለን፡፡

በዓልን አስመልክቶ በመንግስት በኩል የሚደረጉ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሮች በአቅመ ደካሞች ፊት ላይ ትልቅ ተስፋን ሲያሳድሩ ተመልክተናል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ወረዳ አስተዳደር ድረስ የተዘረጋው ይህ ሰንሰለት፣ በዓሉን ማክበር ለሚቸገሩ ወገኖች ማዕድ ማጋራትን ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ ሰንብቷል። የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደሚገልጹትም የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ከአንድ ወቅት ድጋፍ በላይ የከተማዋን ማህበራዊ መሰረት የሚያጠናክር ትልቅ የፍቅር መግለጫ ነው።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “እውነተኛ ብልጽግና የሚለካው በህንፃዎቻችን ቁመት ብቻ ሳይሆን፣ አብሮን ያለውን ደካማ ወገን አንስተን አብረን ለመራመድ ባለን ቁርጠኝነት ነው” በማለት የከተማዋ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች ያላቸውን ተካፍሎ የመብላት ባህል ሲያደንቁ ይደመጣሉ።

አክለውም፣ “አዲስ አበባ የሁላችንም ኩራት የምትሆነው ማንም ሳይራብና ሳይጠማ በዓልን በእኩልነት ማክበር ሲችል ነው” የሚለው ጥሪያቸው፣ ዛሬ በየደጃፉ ለሚታየው የሰብአዊነት ንቅናቄ እንደ ትልቅ ስንቅ ሆኗል። ይህ የከንቲባዋ መልዕክት በህዝቡ መካከል ያለውን የአንድነት መንፈስ ከማጠናከሩ ባለፈ፣ አዲስ አበባን የርህራሄና የሰብዓዊነት መዲና ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን የሞራል ጉልበት ሆኖ ቀጥሏል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ፤ ለማኅበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የሀገር ባለውለታ አረጋውያንና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ማዕድ ማጋራታቸውን አስታውቀዋል።

ይህ ተግባር በከተማችን የማዕከል መስሪያ ቤቶች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እየተከናወነ ያለ በጎ ተግባር ነው ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “በሁሉም በዓላት የምናደርገው የማዕድ ማጋራት፣ ድጋፍ የሚሹ የከተማችን ነዋሪዎችን ‘ምን ጎደለ?’ ብለን በመመልከትና በመጠየቅ ክፍተታቸውን የምንሞላበት፣ ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የገለጽንበት ሰው ተኮር ተግባር ነው” ሲሉም አክለዋል፤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት።

ማዕድ ከማጋራት ባለፈ አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ግጭትና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የሚከሰተውን ጊዜያዊ የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ ጉድለትን ለመሙላት፣ ከፍተኛ በጀት መድበን መሰረታዊ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያደረግን እንገኛለን ብለው፣ በዚህም የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በሰራነው ሥራ፣ በከተማችን የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲሰፍን ተደርጓል ብለዋል።

አዲስ አበባ ለሀብታሙም ለድሃውም፣ ለሁሉም እኩል የተመቸች፣ ስራዎቻችንም ማንንም ያልዘነጉ አካታች እንዲሆኑ እየሰራን ሲሆን፣ ከተማዋ እየተቀየረችና እየተለወጠችበት ያለው ልማት በሰው ኑሮና አኗኗር ላይ ለውጥ እያመጣ ያለ ነው። ‘መስጠት አያጎድልም’ ብለን ባደረግንላቸው ጥሪ መሰረት በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለሚደረገው ማዕድ ማጋራት ለተባበሩን ልበ ቀና ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻቸው ሁሌም እየተሸከሙ በጉልበታቸው በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ላሉ ወጣቶቻችን በሙሉ በራሴና በነዋሪዎቻችን ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉም አክለዋል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በመልዕክታቸው፣ የትንሣኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ፍቅሩን እስከ መስቀል የገለጸበት እና በትንሣኤ የምስራች የተበሰረበት በመሆኑ፣ በዓሉን ስናከብር በታላቅ ፍቅር፣ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖቻችን ያለንን መተሳሰብ በተግባር የምንገልጽበት፣ አንዳችን ለሌላችን የደስታ፣ የሰላም፣ የአብሮነት ምክንያት እንሁን እያልኩ፣ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ ብለዋል።

በእርግጥ ይህ የበጎ አድራጎት ስራ በመንግስት መዋቅር ብቻ የተገደበ አይደለም። በጎ አድራጊ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የየአካባቢው የወጣት ማህበራት፣ ባለሀብቶችና የንግድ ድርጅቶችም የዜግነት ድርሻቸውን በመወጣት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። “ያለኝን ለወገኔ” በሚል መንፈስ የተከፈቱት ደጃፎችና የተዘረጉ እጆች፣ አዲስ አበባ የሁሉንም ደስታ የምትመኝ ከተማ መሆኗን ማሳያ ናቸው።

ወጣቶች በየመኖሪያ መንደሮቻቸው ተደራጅተው፣ እርስ በእርሳቸው በማዋጣትና ከአካባቢው ነዋሪዎች በማሰባሰብ ለአቅመ ደካሞች በዓልን ማክበሪያ የምግብ ፍጆታ ምርቶችን ያቀርባሉ። ምግብ ከማብሰል ጀምሮ፣ የአረጋውያንን ቤት እስከ ማጽዳትና ማደስ ድረስ የሚዘልቅ ተግባር ያከናውናሉ። ከቁሳዊ ድጋፉ ባለፈ፣ በበዓል ቀን ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ከአዛውንቶች ጋር አብሮ በማሳለፍ የሚሰጡት ፍቅር አይተኬ ነው።

ማዕድ ማጋራት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ባይሆንም፣ በአዲስ አበባ ደረጃ እንደ ትልቅ ንቅናቄ መወሰዱ ማህበራዊ ትስስሩን እያጠነከረው ይገኛል። ይህም ከተማዋን የኮንክሪት ህንጻዎች ብቻ ሳይሆን፣ የርህራሄና የሰብዓዊነት መዲና ያደርጋታል። በበዓሉ ወቅት የሚታየው ይህ መረዳዳት በዓል ሲያልፍ የሚቆም ሳይሆን፣ በቋሚነት ለሚቸገሩ ወገኖች ደራሽ የምንሆንበት ባህል እንዲዳብር መነሳሳትን ፈጥሯል። ማዕድ ማጋራት ከአንድ ቀን የምግብ ድጋፍ በላይ፣ “እኔ ለአንተ አለሁ” የሚል የፍቅር ቃል ኪዳን መታደሻ ሆኖ ይገኛል።

በየአካባቢው የሚገኙ የወጣት ማህበራት ይህንን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ተራ ተግባር ሳይሆን እንደ ቅዱስ ተልዕኮ ነው የሚመለከቱት። “በዓል ማለት ለእኛ ለብሶ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ አቅመ ደካማ ጎረቤታችን ስቆ እንዲውል ማድረግ ነው” ይላሉ በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች። ወጣት ሄኖክ በዛብህ እንደሚገልፀው በየደጃፉ እያንኳኩ የሚያሰባስቡት እህልና ዘይት ብቻ ሳይሆን፣ ትውልዱን የሚያስተሳስር ትልቅ የሞራል እሴት ነው።

“መጀመሪያ አካባቢ ሰውን ማሳመን ይከብድ ነበር፤ ዛሬ ግን ነዋሪው ራሱ ደጅ ጠንቶ ‘ማዕድ አጋሩልኝ’ ይለናል” የሚሉት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወጣት ማህበር አባላት በበኩላቸው፣ ተግባሩ በወጣቱና በነዋሪው መካከል የማይበጠስ የመተማመን ድልድይ እንደፈጠረ በኩራት ይናገራሉ። ወጣት አብዱራህማን ሰይድም፣ “ይህ በየመንደሩ የሚታየው የወጣቶች ተነሳሽነት፣ አዲስ አበባን የርህራሄና የወንድማማችነት ህያው ትምህርት ቤት አድርጓታል” ይላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት በከተማዋ እየታየ ያለው የማዕድ ማጋራት ንቅናቄ የከተማዋን ነዋሪዎች የመረዳዳት አቅም ወደ ተደራጀና ውጤታማ ተግባር የቀየረ ትልቅ ስኬት ነው።

“በጎ ፈቃደኝነት የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ሳይሆን፣ የዜግነት ግዴታና የማንነት መገለጫ እየሆነ መጥቷል” የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፣ በተለይም በበዓላት ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከማገዝ ባለፈ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን አንድነትና ወንድማማችነት እንደሚያጸና በአጽንኦት ይናገራሉ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ደረጄ ተሰማም በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ማህበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ የሚቻለው አንዱ ለሌላው ደራሽ ሲሆን ነው። ባለፉት ዓመታት የታየው የዜጎች ተሳትፎና የመረዳዳት መንፈስ አዲስ ገጽታ እየገነባ ይገኛል። ይህ የአብሮነት ድልድይ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሆን የታሪክ አሻራ ስለመሆኑ ያነሳል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡት ሰው ተኮር ድሎች፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከተለመደው የሥነ-ምግባር እሴትነት አውጥተው ወደ ስትራቴጂካዊ የለውጥ መሣሪያነት አሸጋግረውታል።

ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ወዲህ የታዩት የለውጥ ፍሬዎች ዋነኛ መገለጫ የሆነው የበጎ አድራጎት ተግባር፣ የማኅበረሰቡን የአብሮነት ስሜት በመቀስቀስ በዜጎች መካከል የነበረውን የኑሮ ደረጃ ልዩነት በሥራና በመተሳሰብ ድልድይነት አጥብቧል። በከተማዋ ባህል እየሆነ የመጣው ማዕድ ማጋራትና የበጎ አድራጎት ተግባር፣ ማህበራዊ ፍትሕ በንግግር ሳይሆን በተግባር እንዲረጋገጥና ዜጎች በከተማቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ጽኑ መሠረት ጥሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት 13 ቢሊዮን 136 ሚሊዮን 434 ሺህ 921 ብር እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ የአካባቢ ልማት ሥራዎች 2 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን 466 ሺህ 477 በድምሩ 15 ቢሊዮን 336 ሚሊዮን 901 ሺህ 398 ብር በማሰባሰብ ለህዝብ ጥቅም ማዋል መቻሉን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለከተማዋ ምክር ቤት ባቀረቡት የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ 6 ወር አፈፃፀም ሪፖርት አመልክተዋል፡፡

ጉዳዩ ማዕድ ከማጋራት ሻገር ሲልና ከኢኮኖሚ አኳያ ሲታይም፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወነው የ45 ሺህ 566 የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ደሳሳ ጎጆዎችን በአዲስ የመተካት ተግባር፣ በመደበኛው የመንግሥት በጀት ሊሸፈን የማይችልን ግዙፍ ወጪ በሕዝባዊ ተሳትፎ የታደገ ታላቅ የሀብት ምንጭ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ግዙፍ የቤት ግንባታና እድሳት ሂደት፣ በመደበኛ የኮንስትራክሽን ሥርዓት ሊወጣ ይችል የነበረን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማዳን፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለውን የላቀ የሰው ኃይል ኢንቨስትመንት አቅም በተግባር አሳይቷል።

ማዕድ ማጋራት የአንድ ወቅት ኩነት ወይም የዓመት በዓል ትዕይንት ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም የሚለውም የብዙዎች አስተያየት ነው። ዛሬ በየሰፈሩ የሚታየው የወጣቶች መነሳሳትና የመንግስት ድጋፍ፣ ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመገንባት መሰረት ነው። ደስታ የሚረጋገጠው ብቻ በመብላት ሳይሆን አብሮ በመቁረስ በመሆኑ በተግባር የታየው ይህ አጋጣሚ፣ በሌሎች ቀናትም ለጎረቤታችን እንድንደርስ ስንቅ ሊሆነን ይገባል።

አዲስ አበባን የፍቅር ከተማ የሚያደርጋት በህንፃዎቿ መብዛት ሳይሆን፣ በእንዲህ አይነት የማይበጠስ የመረዳዳት ሰንሰለት የታጠረች መሆኗ ነውና ይህ በጎነት ይቀጥል እንላለን።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review