“በባይተዋርነት ውስጥ የነበረችን ሴት ነገዋን ማሳመርን እንደ ትንሳኤ ነው የምቆጥረው”

You are currently viewing “በባይተዋርነት ውስጥ የነበረችን ሴት ነገዋን ማሳመርን እንደ ትንሳኤ ነው የምቆጥረው”

                                                                                          በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ሰልጥና በስራ ላይ የምትገኝ ወጣት  

መራብና መጠማትን ለዓመታት የቅርብ ጓደኛዋ አድርጋዋለች፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ጠግቦ መብላትና የተሻለ ጫማ መጫማት ለእርሷ ቅንጦት ናቸው፡፡ የትምህርቷን ጉዳይ ካነሳች ደግሞ “የምትበላው የላት ትከናነበው አማራት” ይሆንባታል፡፡ ከኢሉባቦር እስከ አዲስ አበባ ድረስ በቤት ሰራተኛነት በተለያዩ ግለሰቦች ቤት ሰርታለች፡፡ “ያሳለፍኩትን ከባድ ጊዜ ተማርኩበት እንጂ ተሰብሬ አልቀረሁበትም” የምትለን ወጣት ቤተልሄም መኮንን (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሟ የተቀየረ) በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የመጀመሪያ ዙር  ስልጠና ሰልጥናለች፡፡

የእናት፣ የአባት፣ የእህትና የወንድም ጣዕሙን ፈፅሞ አታውቀውም፡፡ ‘ቤተሰቤ’ የምትለው ሰው አልነበራትም። ገና በልጅነት እድሜዋ ክፉና ደጉን ለይታ በማታውቅበት ሁናቴ ወላጆቿን በሞት በማጣቷ ምክንያት በአጎቷ ቤት አድጋለች። “አስተምራታለሁ፤ አሳድጋታለሁ ብሎ ኃላፊነት የወሰደው አጎቴ እድሜዬ ለትምህርት ቢደርስም እንኳን አይደለም ለማስተማር ይቅርና ለማኖር ፍላጎቱ ከእለት ወደ እለት እየተቀዛቀዘ መጣ። ይባስ ብሎ በቤት ውስጥ የስራ ጫና በመፍጠር እንድማረርና እንድጠፋ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል” በማለት ቤተልሄም ተናግራለች፡፡

የእኔ የምትለው የቅርብ ቤተሰብ በዙሪያዋ አለመኖሩን ተከትሎ ከአጎቷ ቤት በመጥፋት ሌላ ሰው ቤት ለመስራት ተገደደች፡፡ ረሃብ፣ እርዛት እና የማይነጉ የሚመስሉ ሌሊቶች በጨለማ ሞገዳቸው ቢያስፈራሯት ችግሩን ለመሸሸጊያነት በጊዜያዊ መፍትሄነት የመረጠችው የሰው ቤትን ነበር፡፡

እንደ ወጣቷ ገለፃ፤ የቤተሰብ ፍቅር ማጣት፤ ጣዕማቸውን ለማወቅ እንኳን እድል አለማግኘቷ በህይወቷ ተስፋ እንድትቆርጥ አድርጎታል፡፡ “የኔ ወላጆች በህይወት ኖረው ቢሆን ኖሮ የአማረ ለብሼ፣ ራቤን አስታግሼ፣ ትምህርቴን ተከታትዬ እንዲሁም የወላጅ ፍቅርን ካለማንም ከልካይ የማገኝበት እድል ይኖር ነበር ብዬ አለቅሳለሁ፡፡ በተለይ በቤተሰብ ልዩ እንክብካቤ እና ፍቅር አግኝተው በሚኖሩ ሰዎች ህይወት እቀናለሁ፡፡ የቱንም ያህል ባለቅስ የቱንም ያህል እራሴን ድባቴ ውስጥ ብከትም ያንን የተመኘሁትን ህይወት ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ በትላንትና፤ በይሆን ይሆን በተሟጠጠ ተስፋ ውስጥ መጋለብ ትርፉ መጋጋጥና የቆየ ቁስልን ከመነካካት የተሻለ ትርፍ አልነበረውም” ብላለች፡፡ 

“በሰው ቤት እያገለገልኩ ትምህርቴን ጎን ለጎን ለመከታተል በማደርገው ጥረት ውስጥ አሰሪዎቼ ፍቃደኛ አልነበሩም። አንዳንዴ ለመማር ከነበረኝ ጉጉት የተነሳ ያሰብኩትን ባለማድረጌ አለቅስ ነበር። እራሴን ለማጥፋትም ከአንድም ሁለት ጊዜ ሙከራ አድርጌያሁ” ስትል ወጣቷ የህይወት ውጣ ውረዱ ምን ያህል ወገብ ያጎብጥ፣ ጉልበት ያርድ እንደነበር ተናግራለች፡፡

ቤተልሄም በኢሉባቦር በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራ የምትጫማው ጫማ አልነበራትም፡፡ በባዶ እግር እየተጓዘች የጠዋት ብርዱንና የከሰዓት ሃሩሩን ተጋፍጣ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ጥርሷን ነክሳ ተምራለች፡፡ ይሄ ሁሉ ባለበት ለረጅም ሰዓት ቆማ ስለምትሰራ የኩላሊት እንዲሁም የወገም ህመም ገጥሟት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ወጣት ቤተልሄም ወደ ማዕከሉ የመጣችበትን አጋጣሚ ስታስረዳ እንደገለጸችው፣ በተለያየ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ስልጠና መዘጋጀቱን መረጃ ሲደርሳት እድሉ እንዲያመልጣት አልፈለገችም። በኤሌትሪክና ቧንቧ ስራ ስልጠና ወስዳለች፡፡ “የወንድ ስራ ነው” በሚል በርካታ ሴቶች ስልጠናውን ለመውሰድ አይደፍሩም፡፡ እሷ ግን ይከብደኛል የምትላቸውን ነገሮች የመጋፈጥ ልምድ አላት፡፡ ለቀጣይ ሕይወቷ የተሻለ እድል ማዕከሉ ይዞ መምጣቱ  ብርሃን እንዲፈነጥቅላት አግዟታል፡፡

“በብዙ ውጣ ውረድ እና የህይወትን መራራ ጽዋ ለተጋፈጥን ሴቶች ማዕከሉ ዳግም ተስፋችንን እንድናለመልም አድርጎናል፡፡ በተስፋ መቁረጥና በባይተዋርነት ውስጥ ለነበረች ሴት ተስፋ መስጠት፤ ነገዋን ማሳመር ለእኔ እንደ ትንሳኤ ነው የምቆጥረው፡፡ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከሀጢያት ለማንጻት የፍቅር መስዋዕትነት ከፍሏል፤ የሰው ልጆች መከራም በትንሳኤው ጉልበት ድል ተነስቷል፡፡ ትንሳኤው ከወደቅንበት የተለያየ ችግር መነሳትን ያመላክትልናል። የሰው ልጅ ከወደቀበት ጨለማ ተነስቶ ወደሚደንቅ የብርሃን ጎዳና እንዲጓዝ አምላክ ፈቅዷል፡፡ እኔ የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል የማከብረው ከቁዘማዬ በማገገም ነገን በተስፋ የተሞላ ጎዳና እንደሚጠብቀኝ በማሰብ ነው” ብላለች፡፡

እንደ ወጣቷ ገለጻ፣ ማዕከሉ እንደእሷ ላሉት ሴቶች የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ ነው፡፡ ለስድስት ወር የህይወት እና የስራ ክህሎት እንዲሁም የስነ ልቦና ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከስልጠናው በርካታ ነገር አግኝተናል፡፡ ሴት ልጅ ስልጠናዎችን በበቂ ሁኔታ ካገኘች ከገባችበት ችግር መውጣት፣ በስራዋ ውጤታማ መሆን እና ህይወቷን በተቃናው መስመር ላይ ማስኬድ እንደምትችል ተረድታለች፡፡

“አሁን ላይ በተከራየሁበት ቤት ውስጥ እየኖርኩ እገኛለሁ፡፡ ይህን ለማድረግ የቻልኩበት ደግሞ በማዕከሉ ውስጥ የተሰጠኝን የስራ እድል በመጠቀም ነው፡፡ በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ውስጥ የስፖርት አሰልጣኝ በመሆን እንዲሁም የፋይናንስና ግዢ ክፍል ውስጥ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ የስፖርት አሰልጣኝነቱን ከማዕከሉ ባሻገር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ላይም በማስ ስፖርት መርሃ ግብር ላይ ተገኝቼ አሰለጥናለሁ፡፡ ስራዎችን ብዙ ጊዜ በፍላጎትና ደስተኛ ሆኘ እከውናለሁ፡፡ በተለይ ስፖርቱን መስራቴ የወገብ ህመሜ እንዲታገስል አድርጎልኛል፡፡ ከከባድ የስራ ጫና ማረፍ ስለቻልኩኝ ከህመሞቼ እያገገምኩ እገኛለሁ” ብላለች። 

ነገን ተስፋ በማድረጓ አዲስ ጎጆ ቀልሳ እየኖረች ትገኛለች፡፡ ከ10ኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርት አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ አሁን ባለችበት ሁኔታ እጅግ ደስተኛ እና ተስፈኛ ናት፡፡ አብረዋት ከሚሰሩ ሰዎችም ጋር ጥሩ ተግባቦትን በመፍጠር ስራዋን በውጤታማነት እያስቀጠለች ስለመገኘቷ በቅርበት የሚያውቋት ይመሰክሩላታል፡፡ 

የሺወርቅ ብርሃኑ ትባላለች፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ፀሃፊ ስትሆን ከቤተልሄም ጋር በስራ ጉዳይ የሚያገናኟቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በፍጹም ስነ ምግባርና የስራ ተነሳሽነት ስራዋን የምትወጣ ወጣት ስለመሆኗ፣ “ያላት አቅም ወደ ሌላ የሚጋባ እና በቶሎ የመረዳት አቅሟ ከፍተኛ ነው፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ስራዋን ከዳር ለማድረስ ትሯሯጣለች፡፡ ያሳለፈችው የህይወት መሰናክል መቼም እንደማያቆማት ይልቁኑም ከእለት ወደ እለት እያጠነከራት መጥቷል” በማለት ምስክርነቷን ገልፃለች፡፡

“በማዕከሉ ውስጥ ሰልጥነው የሚወጡ ሴቶች ያሉባቸውን የቀደመ ችግር አራግፈውና በአዲስ መንፈስ ተነቃቅተው ማየትን የመሰለ ነገር የለም” የምትለው የሺወርቅ እንደ ቤተልሄም ያሉ ሌሎች ሴቶችም በዚህ ልክ ለማደግ ሲጥሩ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ከዚህ የበለጠ የስራ እድገት እንደምታገኝም ያላትን ተስፋ ገልጻለች፡፡

የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ሂርጰሳ ጫላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ማዕከሉ በዋናነት ጤናማ፣ ምርታማና የተረጋጋ ከተማን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሴቷ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ማዕከሉ በተለይም በጎዳና ሕይወት፣ በወሲብ ንግድ  እና በሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሰልጣኞች በቅድሚያ የጤና ምርመራ እንዲያከናውኑ የሚደረግ ሲሆን የህይወት ክህሎት፣ የስነ ልቦና እና የሙያ ስልጠናዎችን ያገኛሉ። መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት አንፃርም የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመቆያ ክፍሎች፣ የጤና እንክብካቤ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የሥልጠና ወጪያቸው እንዲሁ ይሸፈንላቸዋል። ስልጠናቸውን ጨርሰው ከማዕከሉ በሚወጡበት ጊዜም ትንሽዬ የማቋቋሚያ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላ ደግሞ የሙያ እንዲሁም የአስተዳደራዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ዋናው አላማ ሴቷ ከነበሩባት ችግሮች ተላቅቃ በሁለት እግሮቿ እንድትቆም ማስቻል ነው፡፡

እስካሁን በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ሂርጰሳ ዶ/ር አስረድተዋል፡፡ በዋናነት በብዙ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የነበሩ ሴቶች ከኢትዮጵያዊ ስርዓትና እሴት ውጪ ሆነው ይሰሩት ከነበረው ስራ ተላቅቀውና ጤናማ በሆነ ስራ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። በላባቸውና በድካማቸው ሰርተው መተዳደር እንደሚችሉ ግንዛቤያቸው አድጓል፡፡ ወንጀልን ከመከላከል አንፃር በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት፣ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን የስርጭት መጠን ለመቀነስ ተችሏል፡፡ በማዕከሉ ጤናማ፣ ምርታማና የተረጋጋ ከተማን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ትልቅ ተሰፋ ሰጪ ስራዎችን እየከወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review