ልጆች የትንሳኤ በዓል በመላው ዓለም የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ እና በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከመድረሱ በፊት ለሁለት ወራት ያክል በጾምና በጸሎት ይቆያል፡፡ ልጆችዬ እኛም በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ትንሳኤ (የፋሲካ) በዓል ምንነት፣ ልጆች በእለት ተዕለት ህይወታቸው ሊተገብሩት ስለሚገባ ጉዳይ የሀይማኖት አባትን ሃሳብ በማካተት እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል፡፡
ቄስ መንግስቴ ዋሴ እባላለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማሪያም ገዳም አገልጋይ ነኝ፡፡ በነገው ዕለት የሚከበረው የትንሳኤ በዓል ለህዝበ ክርስቲያኑ ትልቅ ትርጉም አለው። ትንሳኤ ከፈጣሪ ዘንድ ለሰው ልጆች ተስፋ የተቸረበት ነው፡፡
ልጆችዬ፤ ትንሳኤ ማለት፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሃጢያት የከፈለው የመስቀል ላይ ፍቅር ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሃጢያት ሲል ሞተ፡፡ በሦስተኛው ቀን በታላቅ ኃይልና ብርሃን ከመቃብር ተነሳ፡፡ በዓሉ መነሳቱን የምናከብርበት እንዲሁም እኛ የሠው ልጆች ከአባቱ ጋር የታረቅንበት በዓል ነው፡፡
ፋሲካ (ትንሳኤ)፤ ሞት አልፎ ሕይወት መምጣቱን፣ ጨለማው በብርሃን መተካቱን የሚበሰርበት በዓል ነው፡፡ ልጆችዬ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የሠው ልጆችን የወደደበት የፍቅር ጥግ የተገለፀበት ነው። በዓሉ የብርሃን ቀንን ያመላክተናል። ይህ ሲባልም ህይወት ከጨለማው ወጥቶ በብርሃን የተሞላበትን የተስፋ ጊዜ ያመላክተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ ሞት ተሸንፎ ህይወት የሰለጠነበትን ቀን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ የሠው ልጅ ከሃጥያት ነፃ የወጣበትን ቀን የምናስብበት እና የምናከብርበት በዓል ነው፡፡
ልጆች፤ በዓሉ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች ያደረገውን እርቅ የምናስብበት ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ አግባብ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ለእግዚአብሔር የምስጋናና የክብር ውዳሴ ይደረጋል፡፡ ወንጌል ይሰበካል። በመዘምራን አማካኝነት የውዳሴ መዝሙሮች ይቀርባሉ፡፡
ለ55 ቀናትም ስጋ፣ ወተትና እንቁላል ሳይበላ ከተቆየ በኋላ፤ በትንሳኤ ሌሊት ፆም ስለሚፈታ በደስታ እና በፍቅር ቤተሰብ ተሰባስቦ ይመገባል፡፡
በዓሉ የበለጠ ውብና ደማቅ እንዲሆን ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን ያደርጋል፡፡ አቅም ያለው ቤተሰብም ለልጆች አዳዲስ ልብሶችን ይገዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በበዓሉ ዕለት ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የተቸገረውን መርዳት በስፋት የሚፈጸም ተግባር ነው፡፡ ለተቸገረ መስጠት እግዚያብሔር የሚወደው ተግባር ነው፡፡
ልጆችዬ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የከፈለውን የፍቅር መስዋዕትነት በመረዳት በዕለት ተዕለት ህይወታችሁም ልትተገብሩት ይገባል፡፡
ልጆች ከዚህ በዓል ልትረዱት አልያም በእለት ተዕለት ህይወታችሁ ልትተገብሩት ስለሚገቡ ተግባራት ጥቂት ልበላችሁ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ፍቅር እና እውነተኛ መስዋዕትነትን ነው፡፡ ይህ ሲባል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ስለወደደ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቶናል፡፡ ታድያ ከዚህ መማር ያለባችሁ በትምህርት ቤት ውስጥ አልያም በምትኖሩበት አካባቢ ካሉ ወዳጆቻችሁ እንዲሁም ጓደኞቻችሁ ጋር በፍቅር እና በመተሳሰብ መንፈስ ያላችሁን ተካፍላችሁ መኖር ይገባችኋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል፡፡ ይህም ተስፋንና ዳግም መነሳትን ያየንበት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ተስፋ ሳንቆርጥ ነገን ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ልጆች በትምህርታችሁ ተስፋ ሳትቆርጡ በጠንካራ መነሳሳት ጥናታችሁን በአግባቡ በማከናወን ከሁሉም የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ አቅም እንዳላችሁ ማሰብ እና ለዚህም በርትታችሁ ማጥናት ይጠበቅባችኋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል። ሰላምን የሰጠ አምላክ መሆኑን በማመን ልጆችም ከጓደኞቻችሁ ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላም መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲባል ቂምንና ጥላቻን በማስወገድ የይቅርታን ልብ በተላበሰ አግባብ ጓደኛነታችሁን ማጠንከር ይገባል እላለሁ፡፡
በበዓሉ ቀን የተቸገሩ ጓደኞቻችሁ ወደ ቤት እንዲመጡ በመጋበዝ አስፈላጊውን ነገር ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ የደስታችሁ ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ ልጆችዬ ልባችሁን በፍቅርና በይቅርታ የተሞላ በማድረግ ደስተኛ ህይወትን ከመምራት በበለጠ በእግዚያብሔር ዘንድም ተወዳጅ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፡፡
በሄለን ጥላሁን