የመዲናችን ኪነ ጥበባዊ መረጃዎች

You are currently viewing የመዲናችን ኪነ ጥበባዊ መረጃዎች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል መጽሐፍ፣ ፊልም፣ የሥነ ጥበብ አውደ ርዕይ እና ሙዚቃ ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

በወንድሙ ካባው የተዘጋጀው “የጀርባ ገጾች” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡  ደራሲው ለመጽሐፉ “የጀርባ ገጾች” የሚል ርዕስ የሰጠው፣ በውስጡ የሰፈሩት ጉዳዮች በሙሉ ማኅበረሰቡ ወደ ኋላ የተዋቸውና ያሳለፋቸው ትዝታዎች መሆናቸውን መግለጹን የሁነት አዲስ መረጃ ያሳያል፡፡ ይህ አዲስ መጽሐፍ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን በተለይም የቤተሰብ መስተጋብሮችን፣ የፍቅር ግንኙነቶችን እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታዩ የተማሪና መምህር ግንኙነቶችን የሚዳስስ ነው። ታሪኩ ከቤተሰብ አውድ ተነሥቶ በዩኒቨርሲቲ ምርቃት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በዋግ ሕዝብ ዘንድ የሚታወቁ ለየት ያሉ የግጥም ባህሎችን በመጽሐፉ ውስጥ ማካተቱ ታውቋል። መጽሐፉ የደራሲው የመጀመሪያ የሕትመት ሥራ ሲሆን፣ በቀጣይም ሌላ  መጽሐፍ ለንባብ ለማብቃት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

በተጨማሪም የታዋቂዋ ደራሲ የዝና ወርቁ “እውቀት በጨዋታ” የተሰኘ የልጆች መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ ይበቃል፡፡ መጽሐፉ የቅደመ ህትመት ሽያጭ ላይ ይገኛል፡፡ ደራሲዋ “ልጆች እንዲያነብቡ እንመክራለን፤ በተለይም ከ12 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ለሚገኙ ልጆች የሚሆኑ መጻሕፍት የሉም ሊባል በሚችልበት ደረጃ ላይ ናቸው። በ2004 ዓ.ም ‘መፍቻው እና ሌሎች…’ የሚለውን መጽሐፌን ያሳተምኩት ይኼው ችግር አነሳስቶኝ ነበር። ምክንያቱ ጥናት ባይደረግበትም  ችግሩ አሁንም እንዳለ ነው” ስትል መጽሐፉን ለማዘጋጀት የተነሳችበትን ሃሳብ ገልጻለች። በመሆኑም የመፍትሔ አካል ለመሆን በመወሰን 150 (አንድ መቶ ሃምሳ) ገጽ  መጽሐፍ ማዘጋጀቷልን ገልጻለች፡፡

ፊልም

“ዳሎቪያ” ፊልም ለእይታ ሊቀርብ ነው። ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ በዋና ገጸ-ባህሪነት የሚተውንበት ይህ ፊልም በነገው ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ እንደሚመረቅ ተገልጿል። ከመጪው ሚያዝያ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ሲኒማ ቤቶች ለዕይታ የሚበቃው ይህን ፊልም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያህል ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉ ተነግሯል፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የፊልም ኢንዱስትሪውን ዕድገት ታሳቢ ያደረገው ይህ ሥራ፣ አብዛኛው ቀረጻው የተከናወነው በሻኪሶና አካባቢው እንደሆነ ታውቋል።

የሥነ- ጥበብ አውደ ርዕይ

የእዮብ ኪታባ የስዕል አውደ ርዕይ ለእይታ በቃ፡፡ “ከጣራ በታች” የተሰኘው ይህ የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ የሚገኘው በገብረክርስቶስ ደስታ ሞደርን አርት ሙዚየም ውስጥ ሲሆን፤ እስከ ሚያዝያ 18 ቀን  2018 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል፡፡

በሌላ መረጃ “በሰማይ እና በምድር መካከል” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ የሰዓሊ መላኩ አየለ ስራዎች የቀረቡበት ይህ አውደ ርዕይም እስከ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል፡፡ አውደ ርዕዩ የሚታየው ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል  ሲሆን መግቢያው በእስጢፋኖስ ቤተክርስትያን በኩል ነው፡፡

እንዲሁም  የሰዓሊና ቀራጺ ታምራት ገዛኸኝ ሥራዎች የቀረቡበት “ኩይሳ” የቅርጻ ቅርጽ አውደ ርዕይ  በእይታ ላይ ነው፡፡  ይህ አውደ ርዕይ ከተለያዩ የወዳደቁ  ቁሳቁሶች የተሰሩ ልዩ የጥበብ ውጤቶች ለተመልካች የቀረቡበት  ሲሆን፤ ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት በእይታ ላይ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡ ይህ የቅርጻ ቅርጽ አውደ ርዕይ የሚታየው ብስራተ ገብርኤል፣ ላፍቶ ሞልን አለፍ ብሎ በሚገኘው ሚካኤል ጸጋዬ ክሬቲቭ ስቱዲዮ ነው፡፡

ሙዚቃ

“ባህላችን” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ ስራ ለአድማጭ ተመልካች ሊደርስ ነው፡፡ የመላኩ ሲሳይ (ኢንጅኒዬር) ስራ የሆነው ይህ ሙዚቃ ከሰሞኑ ይፋ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ የዘፈኑ ግጥምና ዜማ የራሱ የመላኩ ሲሳይ ሲሆን ዜማው ደግሞ በእዮኤል መሀሪ ተሰርቷል፡፡ ዘፈኑ ከሰሞኑ በናሆም ሪከርድስ አማካኝነት እንደሚለቀቅም ተሰምቷል፡፡

በጊዜው አማረ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review