ትንሳኤ በትናንት ገጾች

You are currently viewing ትንሳኤ በትናንት ገጾች

ዛሬ ላይ በጋዜጦችና መጽሔት ገጾች ላይ የሚሰፍሩ የበዓላት ዘገባዎችና ኩነቶች፣ የጊዜን መጋረጃ ቀድደው በመሻገር የዘመኑን ሁኔታ ያሳያሉ፡፡ የህትመት ውጤቶቹ የዘመኑን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የአኗኗር ዘይቤ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ የታሪክ ዘጋቢ ጭምር ናቸው፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ፣ በዘመኑ የነበረውን መንፈስና ነባራዊ እውነታ ምን ይመስል እንደነበር ለታሪክ ተመራማሪዎችም ሆነ ያለፈውን ዘመን ለሚመረምሩ ግለሰቦች እንደ ትልቅ የመረጃ ምንጭ ያገለግላሉ። የጋዜጣና መጽሔት ህትመት ዋነኛ ፋይዳውም ይኸው ነው፤ የዛሬን ክስተት ሰንዶ ለነገው የታሪክ ማህደርነት አሻግሮ ማቆየት።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ፣ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል የዘመናትን የጊዜ ሰሌዳ ወደ ኋላ በማሽከርከር የቀደሙ የትንሳኤ በዓላትን ድባብ ዳስሷል። የበዓሉ ዋዜማ ዝግጅት፣ የዕለቱ የበዓል እንቅስቃሴና የበዓሉ ማግስት ትውስታ ምን ይመስል እንደነበር ለማሳየትም በኢትዮጵያ የህትመት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸውን የ‘ብርሃንና ሰላም’ ጋዜጣን፣ ‘መነን’ እና ‘Addis Reporter’ መጽሔቶችን ቃኝቷል። እነሆ በቀድሞ የህትመት ውጤቶች ለንባብ የበቁ የበዓል ትውስታዎች በሚከተለው መልኩ አሰናድተነዋል። ውድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ቤተሰቦች ከቀድሞ ጋዜጣና መጽሔቶች ያገኘናቸው ዘገባዎች የዘመኑን ሁኔታ በሚገባ ስለሚያሳዩ፣ በዘመኑ በተጻፈበት የቋንቋና የአጻጻፍ ዘይቤ እንዳለ ለማውጣት ጥረት አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!

የትንሳኤ በዓል በቀደመው ዘመን

የትንሳኤ በዓል ድምቀትና ትርጉም የሚመነጨው አማኙ ለሁለት ወራት ያህል ከሚያደርገው ጾምና ጸሎት (ዐቢይ ጾም) ጋር ተያይዞ ነው። በዚህ የጾምና የጸሎት ወቅት ሕዝበ ክርስቲያኑ የፈጣሪውን ሕማማትና መከራ በጾም እያሰበ፣ በታላቅ ተመስጦ ወደ ልቦናው ይጓዛል። እነዚህ ለሳምንታት የሚዘልቁ የጸሎትና የሱባኤ ጊዜያትም ማሳረጊያቸው የትንሳኤ በዓል ይሆናል። በመሆኑም ስለ ፋሲካ ስናወሳ፣ ለበዓሉ መገኘት መሠረት የሆነውን የዐቢይ ጾምን መንፈሳዊ ጉዞ አለማስታወስ አይቻልም። ጾሙ ለበዓሉ ድምቀት መንገዱን እንደሚጠርግ ሁሉ፣ ትንሳኤም ለነዚያ የጾምና የጸሎት ቀናት የደስታና የብርሃን ምላሽ ሆኖ ይመጣል። ስለሆነም የቀደሙ የሕትመት ውጤቶች ስለ በዓሉ አከባበር ሲዘግቡ፣ የጾሙንና የጸሎቱን ድባብ ከበዓሉ ሁኔታ ጋር አስተሳስረው ቃኝተዋል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ባለቤት፣ በእቴጌ መነን ስም የተሰየመችውና ከኢትዮጵያ ቀደምት ህትመቶች መካከል አንዷ የሆነችው “መነን” መጽሔት፣ ስለ ትንሳኤ ሰፊ ሐተታ ባስነበበችበት በሚያዝያ ወር 1951 ዓ.ም ዕትሟ ጾሙን የሚያወሳ አንድ መጣጥፍ አስነብባለች፡፡ የመጣጥፉ ርዕስ “የነፍስ መሰላል ጾም” ይሰኛል። “ጾም ለነፍስም ሆነ ለሥጋ ብርቱ ተጠቃሚነት ያለው የተፈተነ መድኃኒት ለመሆኑ የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ይህ አሁን… የጾምነው ዐቢይ ጾም ወይም ሁዳዴ የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ… ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት የጾመው ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የሁላችን ጸላኤ ሠናያት ሰይጣን በትዕቢት፡ በስስት፡ በንፍገት፡ በእነዚህ በሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ሊፈታተነው ቀርቦ ከክርስቶስ ፊት ድል ሆኖ ተመልሷል” ስትል የጾሙ ምንነትና አስፈላጊነት መጽሔቷ በስፋት አስነብባለች፡፡

በቀደምት የህትመት ውጤቶች በስፋት ባይሆንም በጣም ውስን የሆነ ሽፋን ለትንሳኤ በዓል መስጠታቸውን የአዲስ ልሳን ዝግጅት ለመታዘብ ችሏል። አልፎ አልፎም ቢሆን የትንሳኤን በዓል በሚመለከት ሽፋን ከሰጡ ቀደምት የህትመት ውጤቶች መካከል በስፋት ተነባቢ የነበረው “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ ይገኝበታል፡፡ ጋዜጣው በሚያዝያ 23 ቀን 1922 ዓ.ም ዕትሙ፣ “የስቅለትና የትንሳኤ በዓል በግሪክ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ዘገባ አስነብቧል፤ “የአክሱም ጳጳስ ፓትርያርክ ኒኮላ ቀድሞ እዚህ የነበሩት አሁን ደግሞ እንደገና ወደ አዲስ አበባ መጥተው ዓርብ በሦስት ሰዓት በዓለ ስቅለትን ለማክበር ግሪካውያንም ሁሉ በቤተ ክርስቲያናቸው ተሰብስበው መብራት አብርተው ዑደት አደረጉ፡፡ ፓትርያርክ ኒኮላስም ስለ ኢትዮጵያና ስለ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ፣ ስለ ልዕልት ወይዘሮ መነንና ስለ መኳንንቱ፣ ስለ ሕዝቡ ሁሉ ጸሎት አደረጉ፡፡ በበዓለ ትንሳኤም እንደዚሁ በከተማ ያሉ ግሪካውያን ሁሉ ተሰብስበው ፓትርያርክ ኒኮላስ ቀድሰው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ተናገሩና ሕዝቡን ደስ አሰኝተው አሰናበቱት” ሲል አስነብቧል፡፡

በዚሁ ዕትም ላይ በትንሳኤ በዓል ማግስት የእሳት አደጋ ተከስቷል። በጋዜጣው አደጋውን በሚመለከት እንዲህ ሰፍሯል፤ “በሚያዝያ 20 ቀን ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ሱቁን ዘግተው ሠራተኞች ከወጡ በኋላ ሙሴ ኮርስቶና፡ ሙሴ ጆርጂ ካሉ ጆርጥሎስ ወንድማማቾቹ የሚነግዱበት የወይዘሮ በለጥሻቸውና የደጃዝማች መሸሻ ወርቄ ሱቅ ተቃጠለ። የተቃጠለው ዕቃ ሒሳብ እስከ 2 ሺህ ብር ይሆናል፡፡ ትጉሁ ከንቲባ ነሲቡ ዘበኛውን በጥሩምባ አስነስተው ከእሳት ያዳኑት ዕቃ 2 ሺህ ብር ይገመታል። ሲቢርቶ የነበረበት ጓዳ እንዳይቃጠል በጎረቤት የነበሩ ዘበኞች ውኃ እየቀዱ በብርታት ባያጠፉት በተራው ያለ ሱቅ ሁሉ አይተርፍም ነበር።… ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴም እጅግ አዝነውላቸው የተቃጠለውን ሱቅ አይተው አይዟችሁ ብለው ተስፋ ሰጥተዋቸዋል…” በማለት ትንሳኤን ከእሳት አደጋ ክስተት ጋር በማስተሳሰር በጋዜጣው ሽፋን አግኝቷል፡፡ ሌላው ትንሳኤን መነሻ አድርገው የተለያዩ መጣጥፎች ካስነበቡ ቀደምት የህትመት ውጤቶች መካከል አንዱ በጊዜው ተነባቢ የነበረው “Addis Reporter” መጽሔት ነው፡፡ በፈረንጆቹ በሚያዝያ 11 1969 “Easter in Ethiopia” በሚል ርዕስ ስለ ዐቢይ ጾም፣ ትንሳኤና በትንሳኤ በዓል ስለሚደረጉ መሰናዶዎች ጥልቅ ዳሰሳ አድርጓል፡፡ በመጣጥፉ መጀመሪያ ላይ ሰፊ ትኩረት የተሰጠው ኢትዮጵያ ለዘመናት ጠብቃ ያኖረችው ኃይማኖታዊ ትውፊትና በዓሉን ለማክበር መነሻ የሆነው ዐቢይ ጾም ጉዳይ ነው። በዓሉ ለዘመናት የቆዩና በቀላሉ የማይሸረሸሩ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች መገለጫ መሆኑን በመጥቀስ፣ በተለይም ለ56 ቀናት የሚቆየው የእንስሳት ተዋጽኦ አልባ ጾም በበዓሉ ዋዜማ ላይ የሚፈጥረውን ከፍተኛ ጉጉት በመጣጥፉ ትኩረት አግኝቷል። በመጣጥፉ ጾሙ ረዥምና ጥብቅ በመሆኑ ምክንያት በወጣቱና በአዛውንቱ ትውልድ መካከል የሐሳብ ልዩነት እንዳለ ጠቁሞ፣ አብዛኛው ሕዝብ ግን የጾሙን መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴት አክብሮ በጾምና በጸሎት እንደሚቆይ በዝርዝር ያስቃኛል።

በተለይ በዚህ መጣጥፍ አንድ ትኩረት የሚስብና ለዛሬው ዘመን እንግዳ የሚመስል አስገራሚ ጉዳይ በመጣጥፉ ተነስቷል፡፡ ይኸውም በወቅቱ የነበረውን ማህበራዊ ሽግግር አመላካች ወይም “የትውልድ ክፍተት” ጉዳይ በበዓል አከባበር ዙሪያ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እያሳረፈ እንዳለ ተዳስሷል፡፡ በመጣጥፉ እንደሰፈረው፣ በ1960ዎቹ አካባቢ የነበሩ አንዳንድ የተማሩ የሚባሉ የዚያ ዘመን ወጣቶች፣ ለ56 ቀናት የሚዘልቀውን የዐቢይ ጾም ሥርዓት “ከባድ ነው” በማለት ማሻሻያ እንዲደረግ እንደሚጠይቁ አስነብቧል፡፡ እነዚህ ወጣቶች የጾሙን ርዝማኔና ጥብቅነት በምክንያታዊነት ለመተንተንና ምናልባትም “ለውጥ ያስፈልጋል” የሚል መንፈስ ለማሳየት ሲሞክሩ፣ በሌላ በኩል የዚያ ዘመን አባቶችና እናቶች ደግሞ ይህን የዘመናት ትውፊትና የእምነቱን ሥርዓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማክበር እንደሚገባ አጥብቀው መከራከራቸውንም መጣጥፉ አስነብቧል፡፡

በዚሁ የ“Addis Reporter” መጽሔት ዕትም ላይ በዓሉን አስመልክቶ የሚታየውን ደማቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም በስፋት ተዳስሷል። ትንሳኤን ለማክበር የሚደረገው ዝግጅት ከገበያ ግርግር ጀምሮ እስከ ቤት ውስጥ የድግስ መሰናዶ እንደሚዘልቅ ያብራራል፡፡ በተለይም በቅዳሜው ዋዜማ የቤት እመቤቶች የዶሮ ወጥ ለመሥራት የሚያደርጉትን ጥረትና ወንዶች የበዓል በሬና በግ ይዘው ወደ ቤት የሚመለሱበትን ትዕይንት በሥዕላዊ መግለጫ ጭምር አስቀምጦ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ እንደ ጠላና ጠጅ ያሉ የሀገር ባህል መጠጦች መዘጋጀታቸው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅም ቢለያይም ቅሉ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ አቅሙ በደስታና በፍሥሐ በዓሉን እንደሚያከብር መጽሔቱ በዝርዝር አስነብቧል፡፡

ሌላው በሚያዝያ 16 ቀን 1962 ዓ.ም ለንባብ በበቃችው፤ “መነን” መጽሔት የፋሲካ ዋዜማና ዕለትን የሚያስታውሱ የተለያዩ ጽሑፎች ይዛ ወጥታለች፡፡ “ሰም ለበስ” በተሰኘው የመጽሔቷ አምድ ላይ ፋሲካን የሚያስታውስ ወግ በዚህ መልኩ አስተናግዳለች፤ “አንድ ሰው ነበረ፡፡ ፋሲካ በደረሰ ቁጥር ቤቱ ተጋድሞ ያዙኝ፣ ጥለፉኝ እያለ ቤተሰቦቹን ያስቸግራል። ግን ቢያርዱት እንኳን ሐኪም ቤት አይሄድም፡፡ ታዲያ አሁን ባለፈው ፋሲካ ሰሞን እንደልማዱ ተኝቶ ምጥ የያዛት ሴት ይመስል ሲያጓራ የልብ ጓደኛው የሆነ አንድ ሰው ሊጠይቀው መጣ፡፡ የተለመደውን ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ከውጭ የመጣው ሰው እየተገረመ…

 “አምና፣ ካቻምናም በፋሲካ ሰሞን ታመህ ነበር፡፡ አምልኮት አለብህ ልበል?” አለና ጠየቀው፡፡

 “አውቆ በሽተኛው ከአልጋው ቀና ብሎ አጠገባቸው ሌላ ሰው እንደሌለ ካረጋገጠ በኋላ ‘በእውነት የታመምኩ አይምሰልህ’” አለው፡፡

 “ታዲያስ?”

 “ለወላጆቼ፣ ለአያቶቼ፣ ለአማቶቼና ለጡት አባቴ ያክፋይ የሚሉትን ዕዳ መክፈል ሰልችቶኝ ነው ፋሲካ በደረሰ ቁጥር የምታመመው” አለውና ባለቤቱ ብቅ ስትል ተጋድሞ ያቃስት ጀመር – በማለት ቀልድ አዘል የፋሲካ ወግ ዳስሳለች፡፡

ይህ የቀድሞ የህትመት ውጤቶች ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ የትናንት የህትመት ውጤቶች የታሪክ መስታወት በመሆን የበዓላትን ኃይማኖታዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን፣ የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ፣ የትውልድ ሽግግር ፈተናዎችንና የበዓል ትውፊቶችን በሚገባ ያሳያሉ። ትንሳኤ በትናንት ገጾች ሲቃኝ፣ ከኃይማኖታዊ ሥርዓቱ ጥብቅነት ጀምሮ እስከ ማህበራዊ መስተጋብሮችና የቀልድ ወጎች ድረስ ያለው ድባብ፣ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይደበዝዝ እሴት መሆኑን ያረጋግጣል። በመሆኑም እነዚህን የታሪክ ማህደሮች መቃኘት፣ ትናንትን በዛሬው መነጽር አይተን የነገውን ባህላዊና ታሪካዊ እሴታችንን እንድንጠብቅ ትልቅ ትምህርት ይለግሰናል፡፡ መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review