AMN – ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት መርሐግብር ማንችስተር ዩናይትድ እና ሊድስ ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።
ከቦርንማውዝ ጋር 2ለ2 ከተለያየ በኋላ ለ24 ቀናት ምንም ጨዋታ ያላከናወነው ማንችስተር ዩናይትድ በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት ጥሩ ዕድል ተመቻችቶለታል።
በፕሪምየር ሊጉ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር አረጋግጧል።
ዩናይትድ ዛሬ ድል ከቀናው ትናንት በማንችስተር ሲቲ ተሸንፎ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ቼልሲ የሚኖረውን ልዩነት በ10 ነጥብ ያሰፋል። በዚህ ምክንያት ለማይክል ካሪክ እና ተጫዋቾቹ የዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው።
በመጨረሻ ካደረጋቸው ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች አንድ ብቻ ያሸነፈው ሊድስ ዩናይትድም ሦስት ነጥቡ የውድድር ዓመቱን ይቀይርለታል። የዳንኤል ፋርከ ቡድን አሁንም ከመውረድ ስጋት አልተላቀቀም። ቡድኑ ወራጅ ቀጠና ከሚገኘው ቶተንሃም በሦስት ነጥብ ብቻ ይርቃል።

ሁለቱ ክለቦች በቅርብ ዓመታት ባደረጓቸው የሊግ ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ የበላይነቱን ይወስዳል። ቀያይ ሰይጣናቱ ሊድስን በገጠሙበት የመጨረሻ ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አራቱን ሲያሸንፉ በሦስቱ ነጥብ ተጋርተዋል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት በኤላንድ ሮድ ያከናወኑት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ 1ለ1 መጠናቀቁ ይታወሳል። ግጥሚያው ይበልጥ የሚታወሰው የሩበን አሞሪም የመጨረሻ ጨዋታ በመሆኑም ጨምር ነው። ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከዚህ ጨዋታ በኋላ የክለቡን ሃላፊዎች ሸንቆጥ የሚያደርግ አስተያየት ሰጥቶ ለስንብት መዳረጉ ይታወቃል።
የዛሬ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀመራል። በዩናይትድ በኩል በቅርቡ ውሉን ያራዘመው ሀሪ ማጓየር በቅጣት አይሰለፍም። ከጉዳቱ ያገገመው ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ግን ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በሸዋንግዛው ግርማ