ማዕከላቱ ሲፈተሹ

ወጣት ገብረመድህን ንጉስን ያገኘነው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቁጥር 2 በሚገኘው የወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከል ፑል ሲጫወት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሜዲካል ኮሌጅ ትምህርቱን የሚከታተለው ወጣቱ፣ የእረፍት ጊዜውን የሚያሳልፈው ብዙውን ጊዜ በወጣት ማዕከላት በመዝናናት መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል፡፡

“በሰብዕና መገንቢያ ማዕከሉ መገኘቴ በዋናነት ትርፍ ጊዜዬን በየመንገዱ በመዞር በከንቱ እንዳላሳልፍ አድርጎኛል፡፡” የሚለው ወጣቱ፣ አልባሌ ቦታ ሲውሉ የነበሩ ጓደኞቹም ወደ ማዕከሉ እየመጡ በጋራ እንደሚያሳልፉና እያገኙት ባለው አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡

ሌላኛዋ በማዕከሉ በዲጂታል ቤተ መፃህፍቱ ስታነብ ያገኘናት ተማሪ ቃልኪዳን ጌታቸው ናት፡፡ “በቤተ መፃሕፍቱ ውስጥ ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት ስላለ የምፈልገውን ነገር በማውረድ እንዳነብ አስችሎኛል፡፡ የተለያዩ መፃህፍት ስላሉ የንባብ ክህሎቴን አዳብሮልኛል። የኮምፒዩተር አጠቃቀም እውቀቴንም አሻሽሎልኛል፡፡ ከዚህ ቀደም የማነበው ፈተና ሲቃረብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁልጊዜም ለማንበብ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ” ስትል በወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት በመጠቀም ስላገኘችው ጥቅም ገልፃለች፡፡

የዝግጅት ክፍላችን በስፍራው ተገኝቶ ምልከታ ባደረገበት ወቅት በማዕከሉ ከበር ጀምሮ የተተከሉት የተለያዩ የአበባና የፅድ ዛፎች የወጣቶችን ቀልብ በቀላሉ የሚገዙ ሆኖ አግኝቷቸዋል፡፡ ወጣቶች ራሳቸውን በስፖርት ሲያዝናኑ፣ ህፃናቱ ቴኳንዶ ሲሰሩ፣ ሲያነቡ፣ ከረንቡላና የጠረጴዛ ቴኒስ ሲጫወቱ፣ በተለያዩ ኪነ- ጥበባዊ እንቅስቃሴዎች ልምምድ ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡

አቶ አሰግድ ተሾመ የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ማዕከሉ ስራ ሲጀምር መጀመሪያ ወጣቶች ወደ ማዕከሉ እንዲሳቡ ግቢውን የማስዋብና ማራኪ እንዲሆን በትኩረት ተሰርቷል፡፡ በመቀጠል ወጣቶች እንደዝንባሌያቸው እንዲገለገሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን እንዲሟሉ ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ  የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያደረገው ድጋፍም ትልቅ ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ሞዴል የሚባል ሲሆን፣ 18 ዓይነት አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የዲጂታል ቤተ መፃህፍት አገልግሎት፣ የካፍቴሪያ፣ የጤናና የሥነ- ተዋልዶ፣ የገላ መታጠብ አገልግሎት፣ የወንዶች የውበት ሳሎን፣ ጌም ዞን፣ ሳይንስና ፈጠራ፣ የዲ ኤስ ቲቪ፣ የጂምናዚየም፣ የክብደት ማንሳት አገልግሎት፣ እንደ ከረምቡላና ፑል ያሉ የቤት ውስጥ ጨዋታዎች፣ የተለያዩ ክበባት በስፖርት፣ ሰርከስ እና ቴኳንዶ፣ በኪነ- ጥበብ ዘርፉ ውዝዋዜ፣ ዳንስ እንዲሁም በቴአትርና  በመሳሰሉት  አገልግሎት እንደሚሰጥ ነግረውናል፡፡

አቶ አሰግድ እንደገለፁት፣ በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ወጣቱ የአዕምሮ ጤናው እንዲጠበቅ፣ አካላዊ ብቃቱ እንዲረጋገጥ፣ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀና ለወደፊት ሃገር ተረካቢና አምራች ሃይል ሆኖ እንዲወጣ የሚያደርጉ ናቸው፡፡  በአመት አራት ጊዜ፤ ከወላጆች ጋር ልጆቻቸው በወጣት ማዕከላቱ አገልግሎት በማግኘታቸው ያመጡትን ለውጥ በተመለከተ ምክክር ያደርጋል፡፡ በዚህ ከአመት አመት በሚሰጠው አገልግሎት መሻሻል እየታየና ውጤት እየተገኘ ነው፡፡ 

ወጣቶች ራሳቸውን በሰብዕና ከመገንባት በተጨማሪ በማዕከሉ ልምምድ የሚያደርጉት የሃበሻ ሰርከስ ቡድን አባላት በቱርክ ሃገር በተካሄደ የሰርከስ ውድድር በመሳተፍ ውጤት በማምጣት ሀገራቸውን አስጠርተዋል፡፡ ይህም ለሌሎች ትምህርት እንደሚሆን  አቶ አሰግድ ያነሳሉ፡፡  

የወጣት ማዕከሉ ወጣቶች በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን እንዳያሳልፉ ከማገዙም ባሻገር በወንዶች የውበት ሳሎን፣ በጅምናዚየም፣ በገላ መታጠብ አገልግሎት እና በምግብ ዝግጅትና መሰል አገልግሎቶች ለ28 ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡

በክረምቱ መርሃ ግብር በበጎ ፈቃደኛ የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በእንጦጦ ፓርክ፣ በጉቶ ሜዳ እንዲሁም በማዕከሉ ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ ከጤና ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር በኤች አይ ቪ ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ሳምንታትም የጤና ምርመራ መርሃ ግብር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነን ሲሉ  አቶ አሰግድ ነግረውናል፡፡

ሌላኛው ቅኝት ያደረግንበት የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል ነው፡፡ በማዕከሉ ጅም ሲሰራ ያገኘነው ወጣት ኤፍሬም ታመነ፤ “ለስፖርት የተለየ ፍቅር አለኝ፡፡ በወጣት ማዕከሉ እየተገኘሁ ስፖርት በመስራቴ አልባሌ ቦታ ከመዋል እና በተለያዩ ሱሶችና አደንዛዥ እፆች ወጥመድ ውስጥ ከመግባት ታድጎኛል” ሲል ይገልጻል፡፡

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስለማደርግና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ስለምከተል ከተለያዩ በሽታዎች ራሴን መጠበቅ፣ የሰውነት አቋሜ የተስተካከለ እንዲሆንና  በስነ ልቦናም ረገድ የተረጋጋና መልካም አስተሳሰብ እንዲኖረኝ አግዞኛል ሲልም በወጣት ማዕከሉ ያገኘውን ጥቅም ያስረዳል፡፡

“ስፖርትን የህይወታችን አንድ አካል ማድረግ አለብን” የሚለው ወጣት ኤፍሬም፣ በስፖርት ተኮትኩቶ የማያድግ ትውልድ ነገ አምራች፣ ጤናማና በስነ- ምግባር የታነፀ ስለማይሆን ይህን ባህል እናድርገው፡፡ ወጣት ስንሆን ችኩልነት የሚታይበት፣ መጥፎን ከመልካም ለመለየት የምንቸገርበት፣ አቻዎቻችን ያደረጉትን ሁሉ ማድረግን የምንሻበት ጊዜ በመሆኑ ህይወታችንን ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመምራት በወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት በመገኘት መጠቀም እንዳለባቸው ለወጣቶች ምክሩን ለግሷል፡፡

በሰብዕና መገንቢያ ማዕከሉ የካፌ፣ የቤተ መፃህፍት፣ የጂምናዚየም፣ የፑል፣ የጠረጴዛ ቴኒስ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ የሙዚቃና የቴአትር ክበባት፣ የገላ መታጠብ፣ በጤና አገልግሎት የኤች አይ ቪ ምርመራ፣ የወሊድ መከላከያ አጠቃቀም እንዲሁም የምክር አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ምናሉ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ለወጣቶች የመረጃ ማግኛ፣ የመዝናኛ፣ በአካልና በአእምሮ ሰብእናን የመገንቢያ አማራጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡  በስድስት ኪሎ አካባቢ ያሉ አንዳንድ ጫት በመቃምና በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ጊዜያቸውን ሲያባክኑ የነበሩ ወደ ማዕከሉ እንዲመጡ በማድረግ ራሳቸውን የሚለውጡበት መንገድ ተፈጥሯል፡፡

የሚሰጡ አገልግሎቶች ወጣቱን ማዕከል ያደረጉ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ መኮንን፣ በማዕከሉ እያጋጠመ ያለውን የውሃ እና የመብራት መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር መፍትሄ ለማግኘት ጥረት  እያደረጉ እንደሚገኙም ነግረውናል፡፡

የዝግጅት ክፍላችን በሁለቱ የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ተገኝቶ ያነጋገራቸው ወጣቶች ማዕከላቱ ራሳቸውን እንዲያዝናኑ፣ በእውቀት እንዲገነቡ፣ ከተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተላቅቀው በከተማዋ  ልማት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

አቶ ሳሙኤል ምትኩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  የወጣት ሰብዕና መገንቢያ ማዕከል አገልግሎት ልማት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በዘንድሮው ክረምት የወጣት ማዕከላት አገልግሎትን በአግባቡ ለመጠቀም 20 ሺህ የሚደርሱ ወጣቶች በተገኙበት የከተማ አስተዳደሩ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመክፈቻ መርሃ ግብርን አስጀምሯል፡፡

በየወጣት ማዕከሉ የሚሰጡት አገልግሎቶች፣ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ በማዕከሉ ስልጠና እና የማካካሻ ትምህርት፣ ወጣቶች በአካልም ሆነ በስነ ልቦና የዳበሩ እንዲሆኑ የኤች አይ ቪ ምርመራ አገልግሎት፣ የስነ ልቦና ምክር እንዲሁም ከስነ ተዋልዶ ጋር ተያይዞ የስልጠናና የአቻ ለአቻ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡

ከህብረተሰብ አንፃር የተለያዩ በጎ ፈቃደኞች ስላሉ የአረጋውያንን ቤት የማደስ፣ የማዕድ ማጋራት፣ የችግኝ ተከላ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ የወጣቶች የሰብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ውብ፣ ምቹ፣ ሳቢና ማራኪ ለማድረግ በሁሉም ማዕከላት የቀለም እድሳት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት 114 የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ይገኛሉ።

 ማዕከላቱ በሚሰጡት አገልግሎት አነስተኛ፣ መለስተኛ፣ ሁለገብ እና ሞዴል ተብለው በአራት ደረጃ ይከፈላሉ፡፡  ከአራት እስከ አምስት የሚሆን አገልግሎቶችን የሚሰጡት አነስተኛ፣ ከዘጠኝ እስከ 11 መለስተኛ፣ ከ12 እስከ 15 ሁለገብ እንዲሁም ከ16 እስከ 18 አገልግሎት የሚሰጡት ሞዴል ይባላሉ፡፡ በደረጃ ሲቀመጡም አንድ አነስተኛ፣ 19 መለስተኛ፣ 63 ሁለገብ እንዲሁም 22 ሞዴል የወጣት ሰብእና መገንቢያ ማዕከላት ሲኖሩ ቀሪዎቹ ዘጠኙ ደግሞ ያልተመዘኑ ናቸው።

አቶ ሳሙኤል እንደገለፁት፣ የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት ደረጃቸውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ወደ ሞዴል እንዲመጡ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በየአመቱ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስራው አንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚያልቅ ሳይሆን ጊዜን የሚፈልግና አቅምንም የሚጠይቅ ስለሆነ መንግስት ባለው አቅም ማዕከላትን በመገንባት፣ ግብአት እና የሰው ሀይል በማሟላት አገልግሎታቸውን ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ማዕከላቱ ለወጣቶች የመዝናኛና የመረጃ ማግኛ፣ በአካልና አእምሮ ራሳቸውን የሚያጎለብቱበት መድረክ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ ቢሆንም የግብዓት፣ እድሳትና ጥገና እንዲሁም የሰው ሃይል ችግሮች እንደሚታዩባቸው አቶ ሳሙኤል ያነሳሉ። የሰው ሃይል እጥረቱን የተለያዩ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ፣ የግብዓት እጥረትን ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች ድጋፍ በመጠየቅ፣ መፃህፍትን ከግለሰብ እስከ ተቋማት ድረስ የሚሰባሰብበት ፕሮጀክት በመቅረፅና ዲጂታል ቤተ-መፃህፈት በማደራጀት ለመቅረፍ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት፣ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ፣ በተለያዩ ሱሶች እንዳይጠመዱ፣ በአካልና በአዕምሮ የዳበረና የተሟላ ሰብዕና እንዲኖራቸው በመቅረፅ ትልቅ ሚና ያላቸው በመሆኑ የአዲስ አበባን ወጣት በሚመጥን መልኩ እንዲገኙ እየተሰራ ይገኛል። ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ የሚፈልጉትን መረጃ  በሶፍት ኮፒ በስልካቸው አሊያም በኮምፒዩተር አውርደው እንዲጠቀሙ ነፃ የዋይፋይና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ወደ ሳይንስ ካፌ እንዲያድጉ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም እንደ ውዝዋዜ፣ ዳንስ፣ ስነ ፅሁፍ ያሉ የኪነ- ጥበብ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚወዳደሩ ወጣቶችን ማፍራት ተችሏል፡፡ አሜሪካ እና የተለያዩ የአውሮፓ ሃገሮች በመሄድ ውጤታማ የሆኑ የሰርከስ ተወዳዳሪዎችን ከእነዚህ ማዕከላት እየተገኙ እንደሆነ አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል፡፡

ወጣት የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ከ15 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ያለውን እንደሚያካትት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ ሰነድ ያሳያል። ከጠቅላላ የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር ውስጥም 30 በመቶውን እንደሚይዝ “ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ” በተሰኘው ተቋም “ወጣትና ልማት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም የወጣው ጥናት ያሳያል፡፡

ይህ ግዙፍና ወሳኝ የህብረተሰብ ክፍል በከተማዋ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ወጣቱ ጤናው የተጠበቀ፤ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ አምራችና ለሀገር ልማት የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ራሱን በአካልና በአእምሮ የሚያጎለብትባቸው የወጣት ማዕከላቱ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት ይገባል፤ መልእክታችን ነው፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review