AMN – መስከረም 8/2017 ዓ.ም
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ክፍል በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ካሉ ታላላቅ አለምአቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የውጭ ጋዜጠኞችን ሚዛናዊ እና ተጨባጭ የዘገባ ሽፋንን ለማሳደግ አላማ ያደረገ ውይይት አካሂዷል።
ኢትዮጵያ ፈጣን የለውጥ እና ልማት ሂደት ውስጥ እንደመገኘቷ ጋዜጠኞች የተጣራ መረጃ ብሎም ዝርዝር ግንዛቤ ማግኘታቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
መሰል ግንኙነቶች በኢትዮዽያ ላይ ያተኮሩ የዜና ሽፋኖች የኢትዮጵያን እድገት የሚያንፀባርቁ፣ ለፈተናዎቿ እውቅና የሚሰጡ ብሎም መንግሥት ለአካታች እድገት እና ዘላቂ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ እንዲሆኑ ያግዛሉም ተብሏል።
አፍሪካ በአለምአቀፋዊው ሚዲያ የምትሸፈንበት ትርክት በአብላጫው በበሽታ፣ በድህነት፣ በግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት መልኮች ላይ ያተኮረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህ ምስልም በአለምአቀፍ ደረጃ ስለአፍሪካ ያለውን አመለካከት እና የፖሊሲ ውሳኔ እየቀየሰ መቀጠሉ ተመላክቷል።
የዛሬው ውይይትም ሚዛናዊ እና ምሉዕ እይታ ያለው የዘገባ ሥራን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥቶ የተነጋገረ ለወደፊቱም ለዚህ አይነቱ አዘጋገብ መጠናከር መንገዶችን ያመላከተ እንደነበር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡