በወጣቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራና እሴት የመደመርን ጉልበት አይተናል – ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

AMN- ህዳር 4/2017 ዓ.ም

በወጣቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራና እሴት የመደመርን ጉልበት አይተናል ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።

ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮግራም “ክህሎት ኢትዮጵያ” በሚል ስያሚ በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ልህቀት ማዕከል ተጀምሯል።

መርሃ ግብሩን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት እና አንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት በጋራ አዘጋጅተውታል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር)፣ የአንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት መርሃ ግብሩ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ክህሎታቸውን በማሳደግ ከውጪ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን የሚተኩ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን እንዲፈጥሩ የሚደገፉበት ነው።

የክህሎት ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮግራም የይቻላል መንፈስ የተረጋገጠበት ሂደት ነው ያሉት ሚኒስትሯ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት አንዱና ትልቁ ጉልበት በመሆኑ የሁሉንም ትጋት ይጠይቃል ብለዋል።

በወጣቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራና እሴት የመደመር ጉልበት በተግባር መታየቱንም ጠቁመዋል።

ወጣቶች የፈጠራ እምቅ አቅማችሁን ተጠቅማችሁ ከሀገር አልፎ የአህጉሪቱን ብሎም የአለምን ችግር መፍታት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ፈጠራ ላይ እንዲተጉም አሳስበዋል።

የዛሬ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤት ወጣቶች ሌሎችም ይቻላልን እንዲያረጋግጡ ምክንያት በመሆናቸሁ ፈጠራውን በማሳደግ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን ሰጪ እንድትሆንም ወሳኝ ሚና መጫወት አለባችሁ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review