ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለህዝብ ጥቅም መዋል ጀምረዋል – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

You are currently viewing ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለህዝብ ጥቅም መዋል ጀምረዋል – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

AMN – ጥር 16/2017 ዓ.ም

ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለህዝብ ጥቅም መዋል መጀመራቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የተገነባውን የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካን መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዛሬውና ለመጪው ትውልድ የሚጠቅሙ ትላልቅ የልማት አሻራዎች መቀመጣቸውን ጠቁመዋል።

የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተተገበረ ነው ብለዋል።

በዚህም የህዝብን ተጠቃሚነት፣ የሀገርና የክልሉን ኢኮኖሚ ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

የክልሉን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሪዞርቶችን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ አገልግሎት መግባታቸውን አመላክተዋል።

ክልሉ በግብርና ልማት በስፋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ እምቅ የማዕድን ጸጋ የሚገኝበት መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ሀገር ለማዕድን ዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ተደብቀው የቆዩ የከበሩ የማዕድን ጸጋዎች ለህዝብ ጥቅም መዋል መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት በክልሉ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ መንግስት ጸጋን መለየት እና ሀብት መፍጠር ላይ ስኬታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

የፋብሪካው መገንባት ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ጫናን የሚቀንስ መሆኑንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትና ለበርካታ ዜጎችም የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review