AMN- የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም
ሙሉ ስሙ ኤንደሪክ ፌሊፕ ሞሬራ ዴ ሱሳ ይሰኛል፤ የተወለደው በፈረንጆቹ 2006 ብራዚል ታጉአቲንጋ በሚባል የሀገሪቱ ክፍል ነው፡፡
እድሜው አራት ዓመት ሲሞላ ኳስ ማንከባለል ጀመረ፣ የልጃቸውን ድንቅ ችሎታ የተመለከቱት ወላጅ አባት ደግሞ ዘወትር እንቅስቃሴውን እየቀረጹ ፈላጊ ክለቦች እንዲያዩት በማሰብ በዩ ትዩብ ያስጭኑት ነበር፤ ታዳጊው በኳስ ጨዋታው አባት ደግሞ እየቀረጹ በማስተላለፍ እስከ 11 አመቱ ድረስ ዘለቀ፡፡
ነገር ግን በዚህ ወቅት ታዳጊው ፈተና ውስጥ ወደቀ፤ ወላጅ አባት እና እናት ስራም ቤትም ያልነበራቸው በመሆኑ ለጎዳና ህይወት ተጋለጠ፤ ለስድስት ወራትም በማሳደጊያ ማእከል ገበቶ ለማሳለፍ ተገደደ፡፡
በዚህ ጊዜም ለራሱ አንድ ቃል ገባ፤ በእግር ኳስ ገፍቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ ወላጆቹን ከድህነት ለመታደግ ፤ ታድያ በዚህ ጊዜ የታዳጊውን ችሎታ የተመለከተው የብራዚሉ ታላቅ ክለብ ፓልሜራስ አስፈርሞት ከወጣት ቡድኑ ጋር እንዲቀላቀል አደረገ፡፡
በክለቡም ችሎታውን በስልጠና እያሳደገ እስከ 2022 በዚያው ቆየ፡፡

በፓልሜራስ ወጣት ቡድን ባደረገው የስድስት ዓመታት ቆይታ በ169 ጨዋታዎች 165 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ድንቅ አጥቂ መሆኑን አሳይቷል፡፡
ቀጥሎ ዋናውን ቡድን መቀላቀል ቻለ፤ በሁለት ዓመታት ቆይታውም በከለቡ ማልያ 66 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 18 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኘ፡፡
ኤንደሪክ ቀጥሎ በዓለማችን ታላቅ ክለብ እይታ ውስጥ መግባት ቻለ፤ የአውሮፓው ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ባለፈው የውድድር ዓመት በ35 ሚሊየን ዩሮ እንዲሁም በሂደት እየታየ በሚጨመር የ25 ሚሊየን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ ተጨዋቹን አስፈረመ፡፡
በነጩ ማልያም 15 ጨዋታዎችን ሲያደርግ በትናንትናው እለት በኮፓ ዴል ሬ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ማድሪድ ሪያል ሶሲዳድን 1ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አገናኝቷል፡፡
አጥቂው በምሽቱ ጨዋታ ኮከብ ሆኖ መመረጡንም ቢቢሲ ስፖርት ነው የዘገበው፡፡
በልጅነቱ ማድሪድን እየደገፈ ያደገው ተጨዋቹ፣ ክርስትያኖ ሮናልዶ የሱ ቀዳሚ አርአያው መሆኑም ይነገራል፡፡
በሎስብላንኮዎቹ ቤት ጥሩ ጅማሮን እያደረገ ያለው ወጣቱ አጥቂ ኤንደሪክ ከክለቡ ጋር በርካታ ስኬቶችን ይጎናጸፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በበላይነህ ይልማ